በትግራይ ክፍለ ሀገር፣ ዘንጉዊ በሚባል አገር አንድ ሽማግሌ መኳንንት ከሴት ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር፣ ይላል አፈ ታሪካችን፡፡

አንድ ዕለት እቺ ልጃቸው የወደደችውን ወንድ በጭድ ስር ደብቃ ወደ ቤትዋ አስገባችው (እዚያ ጭልጥ ያለ ባላገር ውስጥ አልቤርጎ የለማ!) በዚህ ዘዴ እያስገባች ስታሳድረው አረገዘችለት፡፡ በዚያን ዘመን የሴቶቹ ልብስ በጣም ሰፊ እና ረጅም ሆኖ፣ ሴቲቱ ነብሰጡር ትሁን ወይስ ድንግል አያስታውቅም፡፡ አባትዋ ሳያውቁባት ቀንዋ ደረሰና አክስቷ ቤት ሄዳ ወንድ ልጅ ተገላገለች፡፡

እዚያው አክስትዋ ቤት እያደገ ስድስት አመት ሲሆነው ከልጆች ጋር ሲጫወት አያቱ አዩት፡፡ ፈጣን ነው ነቄ ጉልቤ! ሲያዩት የሚያስደስት፡፡ “ዋ! ምነው ፈጣሪ በፈቀደና ይሄ ጎበዝ ልጅ የልጄ ልጅ በሆነ!” ሲሉ ምኞታቸውን ተናገሩ፡፡ አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች ይህን ለልጃቸው አክስት ተናገሩ፡፡

አክስት ልጁን ወስደው ለአያትየው አስረከቡ፣ የምስራች እልል እያለ፡፡ አያት ቆፍጣና ጀግና ይሆንላቸው ዘንድ በጥንቃቄ አሳደጉት፡፡ ሲጎረምስ የጎበዝ አለቃ ሆነ፡፡ ሲጎለምስ የሰራዊት አለቃ ሆነ፡፡ የፉከራ ስሙ “ስሁል!” (የተሳለ ወይም ስለታም) ሆነ፡፡

ጎንደር ዋና ከተማ ውስጥ በልዑላን መካከል እኔ እነግስ እኔ እነግስ ፍጥጫ ሆነ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይነሳ የሰጉ ተቆርቋሪዎች ለራስ ስሁል ሚካኤል ላኩባቸው፡፡ ሰውየው ትልቅ ሰራዊት በትግሬ መጮህያ በኩል አስገቡና ወድያው ጎንደርን ቁጥጥራቸው ስር አዋሉ፡፡

አዋቂዎችን ለስብሰባ ጠሩ፡፡ ንጉሱን ብገድለውስ? ሲለ ጠየቁ፡፡

“የንጉስ ደም ያፈሰሰ እንኳን እሱ ዘሮቹ ለሰባት ትውልድ አይነግሱም” አለዋቸው፡፡

አንድ ከይሲ ደብተራ ግን መጣና ለብቻቸው “ደም ማፍሰስ አያስፈልግም’ኮ “በሻሽ አንቆ ማሰናበት ይቻላል” አላቸው፡፡

አፄውን በሻሽ አንቀው ገደሉትና አፄ ሆነው ለመቀባት ወደ ማርያም ፅዮን ገሰገሱ፡፡

ካህናቱ “አትነግስም ደም አፍስሰሀል” አለዋቸው፡፡

“እኔ ደም አላፈሰስኩም፡፡ በሻሽ ነው ያነቅኩዋቸው፡፡”

በሻሽ ሆነ በሰይፍ መግደል ያው መግደል ነው ተባለ፡፡ ኩም ብለው ወደ ጎተራቸው ተመለሱ፡፡

አሰቡበትና “መንገስ ባልችል ማንገስ እችል የለ?” ብለው ወስነው፣ አንድን ደስ ያላቸውን ልዑል አነገሱ፡፡ ሁለት ሶስት አመት ከነገሰ በኋላ “የሚገዙት ግን ስሁልነታቸው ናቸው የታወቀ ነው” ወይ ስላስቀየማቸው ወይ ስለሰለቻቸው አወረደትና ሌላ ልዑል አነገሱ፡፡ አንዱን ልዑል’ማ በድጋሚ አነገሱት! ስሁል ሚካኤል እንዲህ አገር አንቀጥቅጠው እየገዙ እያለ፣ የጎጃሙ አገረ ገዥ “አሻፈረኝ! ከዛሬ ጀምሮ አንድ ግብር አልከፍልም፡፡ አገሬን እኔው ራሴ ነኝ የምገዛው” ሲል ላከባቸው፡፡

“ክተት ሰራዊት! ምታ ነጋሪት!” ብለው ወደ ጎጃም መረሹ፡፡ ሰውየው ለራሳቸው ድል ሆነው የማያውቁ አደገኛ ጄኔራል ናቸው፤ ብዙም ሳይዋጉ አመፀኛውን ድል መቱትና ተማረከ፡፡

ስሁል ሚካኤል አይቀጡት ቅጣት ሲቀጡት፣ በቁሙ ህያው እያለ ቆዳውን አስገፈፉት፡፡ ቆዳው ሰው እስኪመስል ጭድ ጠቀጠቁበት፡፡

ፈጣን መልዕክተኞች መርጠው “ንጉሰ ነገስቱ ስጋት እንዳያድርባቸው፣ በተቻለ ፈጥናችሁ ይህን ግዳይ አድርሱላቸው፡፡ ሰራዊታችን ቀስ ብሎ ይደርስባችኋል”

ከእንግዲህ ማን ያበደ ነው ስሁል ሚካኤልን የሚቃወም? እሳቸው አላወቁትም እንጂ በአንድ ሰው ደም የመጀመርያውን ቀይ ሽብር አካሄዱ (ህዝብ ሲበዛ ጊዜ ጓድ ሊቀ መንበር መንግስቱ ኃይለማርያም “ቀይ ሽብር ይፋፋም!” ብለው አውጀው ብዙ ሰው አለቀ – በሳቸው ግምት ሶስት ሺ ሰው ሞተ)

ስሁል ሚካኤለ አንዲት ባርያ ነበረቻቸው፡፡ የሷ ልጅና የሳቸው ልጅ አብሮ አደግ ናቸውና በጣም ይዋደዳሉ፡፡ አንድ አጉል ቀን ጓደኛሞቹ ይጣላሉ፡፡ ያባቱ ልጅ ነውና የስሁል ሚካኤል ልጅ ቀድሞ ጦር ወርውሮ ገደለው፡፡

የሟች እናት ከሰሰች፡፡ ግን ማን ደፍሮ በስሁል ሚካኤል ልጅ ላይ ይፈርዳል? ግድያው ትክክል ነው እያለ ሲፈርድ፣ ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክሷን ቀጠለች፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ፍርድ ገምድል ሲሆንባት ጊዜ ስሁል ሚካኤል ላይ ከሰሰች፡፡

ስሁል ሚካኤል ልጃቸውን አስጠሩት፡፡ መግደሉን አመነ፡፡

“ህጉ ምን ይላል? የገደለ ይሙት አይደለም?”

“ይላል”

“እንግድያው ሞት ፈርጄብሀለሁ” አሉትና በስቅላት ተገደለ፡፡ …

… ስሁል ሚካኤል አገር ሰጥለጥ አድርገው ሲገዙ በጣም ሸመገሉ፣ ወደ መጃጀት ደረሱ፡፡ አንድ ቀን ከታማኞቻቸው ጋር ተቀምጠው ሲመክሩ እንቅልፍ አሸለባቸው፡፡

ብንን ብለው ነቁና “እናንተ፣ ዛሬም እኛ ነን ስልጣን ላይ ያለነው?” ሲለ ጠየቁ፡፡

“አዎን ጌታዬ” አለዋቸው

“አቤት ጠላቶቻችን ምንኛ ይከፋቸው!” አሉ በሀዘኔታ፡፡

ያነበብነው በልባችን ያሳድርልን አሜን!

©ስብሓት ገ/እግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply