በእግዚአብሔር አምናለሁ … ፓርቲው ደግሞ እግዚአብሔር የለም ይላል … ስለዚህ እኔ ለመንግሥት በመሥራት ማገልገል እንጂ በሃይማኖቴ ምክንያት የፓርቲው አባል ልሆን የተፈቀደልኝ አይደለሁም።

ዘነበ ወላ፦ “ጋሼ፣ የማርክስን ፍልስፍና አንብበው የሰው ልጆች አልተረዱትም ወይስ ተግባራዊነቱ ላይ ነው ያልሰመረላቸው?”

ስብሐት፦ “ይኸውልህ፣ እንደ ማነኛውም ወንጌል ነው የማርክስ ወንጌል። ለድሆች ደህንነት የቆመ ነው። ከኢየሱስ ወንጌል የሚለየው በአንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም ገነትን እዚሁ መሬት ላይ እንዘረጋለን ይልሃል ማርክስ። ሠራተኛው መደብ ያሸንፋል ነው ትንቢቱ። አብዮታዊ ፓርቲ ለጭቁኑ አገልግሎት ነው የሚዋቀረው።”

ዘነበ ወላ፦ “ለተከተሉት ሰዎች የማርክስ ፍልስፍና በተግባር ሊተረጎም ይችላል ነው የምትለኝ?”

ስብሐት፦ “ሊተረጎም ካልቻለ የማይቻል ቢሆን እኮ ነው። እንጂ ማርክስ ሃሳቡ በጣም ልክ ነበር። ሃሳቡን እንይ። ከሁሉም እንደችሎታው ለሁሉም እንደሚያስፈልገው ነው የሚለን። ኅብረተሰብ እንደ አንድ ሰው ሆነ ማለት ነው። ሀብቱ በሙሉ የጋራ ነው። ለማንም አናዳላም። ድል ስናደርግ መደብ አይኖርም ወገን አይኖርም። እንደዛ ነው ትንቢቱ። ለእኔ ህልም ነው። ግን ሰው ያለ ህልም አይኖርም።

‘እኔ ቀርቶ እኛ ሆኗል’ በማለት ማርክሲስት ነን የሚሉ ፓርቲዎች አዲስ ገዢ መደብ ሆኑ። ምንም አልተለወጠም። እነሱም የሚፈልጉትን ያገኛሉ ህዝቡም ለጥቂቱ ነገር ይሰለፋል። ‘ይበልጥ ሲለወጥ ይበልጥ ያው ነው’ ይለናል ፈረንሳይ።

የአሜሪካ ሠራተኞች ግን ማርክሲዝምን በሥራ ላይ አዋሉት። ተደራጁ። ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር በሥራ ማቆም አድማ ጠየቁ። የሥራ ሰዓታቸው በቀን 8 ሰዓት ብቻ እንዲሆን ታገሉና አሸነፉ። ዝቅተኛው የቀን ሠራተኛ ደመወዙ በቀን ቢያንስ 10 ዶላር እንዲሆን ሠራተኛው በጥፋት ካልሆነ ከሥራው ቢሰናበት ካሣ እንዲያገኝ የተደረገው በአሜሪካን ሀገር ነው። በእስፖንዳ ማርክሲዝምን በደንብ ተጠቀሙበት።”

ዘነበ ወላ፦ “የፓርቲ አባል ነበርክ?”

ስብሐት፦ “የፓርቲ አባል አልነበርኩም! ብሆን ጥሩ ነበር። እኔ ግን ‘atheist’ አይደለሁም … በእግዚአብሔር አምናለሁ … ፓርቲው ደግሞ እግዚአብሔር የለም ይላል … ስለዚህ እኔ ለመንግሥት በመሥራት ማገልገል እንጂ በሃይማኖቴ ምክንያት የፓርቲው አባል ልሆን የተፈቀደልኝ አይደለሁም አልኳቸው። ተውኝ።”

ዘነበ ወላ፦ “የማሌ ጥናት ተብሎ በየመሥሪያ ቤቱ የውይይት ክበብ ስብሰባ ይካሄድ ነበር። በውቅቱ እንድትሳተፍ ተጠይቀህ አታውቅም?”

ስብሐት፦ “ምንድነው ማሌ?”

ዘነበ ወላ፦ “የማርክሲስት ሌኒንስት ፍልስፍና ውይይት”

ስብሐት፦ “በፍጹም። እነሱም አያስገድዱኝም። እኔም አልቀላቀላቸውም። ሰውየው ካርል ማርክስ አሪፍ ፈላስፋ ነበር። ሰዎቹ ግን ሳይገባቸው ፈተፈቱት። ፍትፈታውንም ውይይት ክበብ አሉት።”

ዘነበ ወላ፦ “የቤተ ክህነት ሰዎች መጥተው አቶ ስብሐት ይምጡ እስቲ ዘር ማንዘሮት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ ነበሩ። እርሶም የዘር ማንዘሮን ክርስትያናዊ ግዴታ ለመወጣት ቤተክህነቷ ትፈልጎታለች። መጥተው ያገልግሏት ቢሉህስ?”

ስብሐት፦ “የእኔን ተፈጥሮ ልብ በል። አንድ ‘formula’ ተከትሎ ያችኑ መደጋገም ደስ አይለኝም። በክርስትና በእስልምና በፖለቲካ ፓርቲም እያልክ ብታጠናቸው አማኞቻቸውን ደንግገው የሚይዙበት ሕግጋት አላቸው። ያ ደግሞ ሼል ሆኖ እንደ ዕንቁላል ቅርፊት ሌላን የምታይበትን ዓይን ይጋርድሃል። ስለዚህ ምንም ዓይነት የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ድርጅት ተከታይ መሆን አልፈልግም።

አባቶችን፣ ቤተክህነትን ማገልገል ከአማኝ የሚጠበቅ ነው … እናንተም ከልባችሁ ቤተክህነቷን እያገለገላችኋት ነው … እኔም እንደናንተ እንዳላገለግል ‘atheist’ ነኝ እላቸዋለሁ።”

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply