Page 1 of 1

የፍልስፍና እና የሳይንስ ወጎች – ካነበብኩት

Posted: Tue Oct 07, 2025 1:00 pm
by yaman

ሶቅራጠስ እስከ ሽምግልና እድሜው ድረስ ወጣቶችን ሰብስቦ ሲያስተምር ኖረና በመጨረሻ ሀሳብን እንደጦር በሚፈሩ የዘመኑ ልሂቃን ክስ ቀረበበት። ወንጀሉ? የወጣቶችን አእምሮ መበከልና መናፍቃዊነት። በዘመኑ የዚህ ዓይነት ክስ ለሚቀርብባቸው ዜጎቿ አቴንስ ሁለት ምርጫ ትሰጣለች – አገር ለቆ መውጣት (ኤግዛይል) ወይም ፍርድ። ሶቅራጠስ ያጠፋሁት አንድም ነገር የለም፣ የምወዳትንና እድሜ ልኬን ያገለገልኳት አገሬን ጥዬ የትም አልሄድም የፈለጋችሁትን ፍረዱ ብሎ ፍርዳቸውን ለመጋፈጥ ወሰነ። ዳኛ ፊት ቀርቦ መሰረተ ቢስ ክሶቹን አንድ በአንድ ከጥልቅ ፍስልፍና ጋር አስረዳ። የአቅም ጉዳይ ሆኖ አጥጋቢ ሆኖ አላገኙትም። በዘመኑ የአቴንስ ባህል መሰረት ጥፋተኛ ነው አይደለም የሚለው የሚወሰነው በዴሞክራሲያዊ ድምፅ አሰጣጥ ነበርና ጥፋተኛ ነው የሚለው በዝቶ ሃምሎክ የሚባል መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት ተደረገ። (በዚህ ምክንያት የሶቅራጠስ ተማሪ የነበረው ፕላቶ ዴሞክራሲን አይወድም። ለፕላቶ ከዘውጋዊ፣ ከአምባገነናዊና ከወታደራዊ ስርዓትም የከፋ የመጨረሻው መጥፎ ስርዓት ዴሞክራሲ ነው። ሞብ ሩል (የመንጋ ስርዓት) ይለዋል። የዴሞክራሲ ትርጉምና ባህሪ ያኔና ዛሬ የተለያየ መሆኑን አንባቢ ልብ ሊል ይገባል!) ፍርዱ ከተወሰነ ብኋላ መርዙን ጠጥቶ እስኪሞት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሶቅራጠስ ያወራቸው ፍልስፍናዎች ዓለምን እስከዛሬ ድረስ ይንጧታል። ለብዙ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች (ሴኔካ፣ ሲሰሮ፣ ጋሊልዮ፣ ወዘተ) ደግሞ ተምሳሌት ሆኖ ሞትን ሳይፈሩ ላመኑበት እስከ መጨረሻ ድረስ መቆም እንደሚቻል የሚያስታውስ ፅናት ነበር። ዛሬ ከማንም በላይ ገዝፎ የሚታየው ሶቅራጠስ ነው። ከሳሾቹ፣ ፈራጆቹና ገዳዮቹ ደግሞ እንደ ጧት ጤዛ ያኔ ረግፈው ወዲያው ተረስተዋል።


ሳይንስ ዛሬ ዓለምን በመዳፉ ስር ከማስገባቱ በፊት፣ ኋላቀርና ልማዳዊ አስተሳሰብ ከሚያራምዱ የጭለማ ሃይሎች ጋር እልፍ አእላፍ ጦርነቶችን አካሔዷል። ህዝብን በሀሰት እያወናበዱ የሀብትና የዝና ምንጫቸው ካደረጉ ከተደራጁ ሀይሎች ጀምሮ፣ አዲስ ሀሳብ እንደጦር እስከሚፈሩ ተራ ግለሰቦች ድረስ ሳይንስ ብዙ ጦርነቶችን አሳልፏል። ለምሳሌ በ7ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ሙስሊሞች ግብፅን በቁጥጥራቸው ስር ሲያስገቡ፣ በአሌክሳንድርያ ቤተመፃህፍት ይገኙ የነበሩ የጥንት የፍልስና፣ የሳይንስ፣ ወዘተ መፃህፍቶች በመሪያቸው ካሊፍ ኡማር ትዕዛዝ አማካኝነት እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ካሊፍ ኡመር ያስተላለፈው ትዕዛዝ እንደ ፈላስፋው ሩሶ አገላለፅ የሚከተለው ነበር ፡ “If the books of this library contain matters opposed to the Koran, they are bad and must be burned. If they contain only the doctrine of the Koran, burn them anyway, for they are superfluous.“

(እነዚህ መፃህፍት በውስጣቸው የያዙት ነገር ከቁርዓን ጋር የሚጋጭ ከሆነ መጥፎ ናቸውና መቃጠል አለባቸው። በውስጣቸው የያዙት የቁርዓን ዶክትሪን ብቻ ከሆነም አላስፈላጊ (ተገዳዳሪ) ናቸውና መቃጠል አለባቸው።)

በዚህ ድርጊት ምክንያት እውቀት ተጨናግፎ ለ1ሺ ዓመታት የሰው ልጅ በጭለማ ውስጥ ኖረ። በሙስሊም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች አማካኝነት ከቃጠሎው የተረፉ ጥቂት ስራዎች ተገኝተው ሳይንስም ፍልስፍናም ከወደቁበት ዳግም ተነስተው ማንሰራራት የቻሉት የአብርሆት ዘመን ተብሎ በሚታወቀው በ17ኛውና 18ኛው ክ/ዘመን ነው። ለዚህ መዘግየት ዋንኛ ምክንያቱ ደግሞ ከእስልምና ብኋላ የበላይነትን ተቆናጥጦ ዓለምን ሲንጥ የነበረው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ነው። ፈላስፋው ሩሶ የካቶሊክ ጳጳሳት ከካሊፍ ኡመር የተሻሉ ሳይሆኑ የባሱ እንደሆኑ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡ “… suppose Gregory the Great was there instead of Omar and the Gospel instead of the Koran. The library would still have been burned, and that might well have been the finest moment in the life of this illustrious pontiff.” (ትርጉሙ ይለፈኝ!)

በቅደመ ሶቅራጥስ ዘመን የፓይታጎረስ ተከታይ የነበሩ ፈላስፋዎች የሰው ልጅ (ወይም መሬት) የዓለማት ማዕከል አይደለም የሚሉ (eg. Philolaus) ፣ የሁሉም ነገር መሰረቱ ፊዝካሊ ኢንዲቪዝብል የሆኑ ነገር ግን ጂኦሜትሪካሊ ዲቪዝብል የሆኑ አተም-ኦች ናቸው የሚሉ (eg. Democritus, Leucippus) እና ሰው ከእንስሳት ኢቮልቭ ያደረገ ፍጡር ነው የሚሉ (eg. Anaximander) የተለያዩ ፈላስፋዎች ነበሩ። ከ2ሺ ዓመታት ብኋላ ግን እነዚህ ተመሳሳይ ሀሳቦች ዳግም በሳይንቲስቶች (በነጋሊልዮ፣ ዳርዊንና ሌሎችም) ሲነሱ ለእስራትና ለጥቃት ያጋልጡ ነበር፣ የካቶሊክ ቤ/ያን በዘረጋው ሲስተም ምክንያት! ዛሬ እዚህ ለመድረስ በርካታ ሊቃውንት መስዋዕት ሆነዋል።


ከላይ የተጠቀሰው የአብርሆት ዘመን ዘግይቶም ቢሆን ጮራውን መፈንጠቅ የጀመረው ከበርካታ የነፃነት ተጋድሎና የፖለቲካ ስርዓት መሻሻሎች ብኋላ ነው። ለምሳሌ በኢንግሊዝ የነበረው ዘውዳዊ ስርዓት በፓርላመንታሪያን ሀይሎች ተንኮታኩቶ አዲስ ስርዓት የተዘረጋው እኤአ ከ1688 ዓም ጀምሮ ነበር። ይህ በተወሰነ ደረጃ ለFree Thinkers (አሰላሳዮች) የተወሰነ ነፃነትን አጎናፅፎ የምርምርና የዕውቀት ስራዎች ከአንዱ ወደ ሌላው በነፃነት እንዲዛመቱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ለፓርላመንታሪያን ሀይሎች ጉልበት የሰጣቸው ነገር ቢኖር ደግሞ ምናልባት የማርቲን ሉተር የፕሮቴስታኒዝም ሪፎርም (Reformation) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሳይሆን አይቀርም። የዚህ ሪፎርም እንቅስቃሴ የተጀመረው ማርቲን ሉተር “The Ninety-five Thesesን” በፃፈበት እኤአ በ1517 ዓም ነው ተብሎ ይታመናል። ከዛ በፊት (ከበርካታ ዓስርት ዓመታት በፊት) በአገራችን በአፄ ዘርዓ-ያቆብ ዘመነ መንግስት (1426-1460 ዓም) ተመሳሳይ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በእነ ደቂቀ-እስጢፋኖስ አማካኝነት ተካሂዶ እንደነበር ከፕ/ር ጌታቸው ድንቅ ስራ አንብበናል። በዛን ወቅት ተራ መኖክሴዎች ለተሀድሶ ተነስተው፣ በዝባዥ ተቋማትንና ስርዓቶችን ባደባባይ እያወገዙ ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ችለው የነበረ ቢሆንም፣ ሆድ አምላካቸው የነበሩ የቤ/ክ/ያን መሪዎች ከንጉሱ ጋር በመመሳጠር የእንቅስቃሴውን መሪዎችና ታማኝ ተከታዮቻቸው በተለያዩ አረመኔያዊ እርምጃዎች ድራሻቸውን አጥፍተዋቸዋል። አገሪቱን ከተኛችበት የሚቀሰቅስና በባዕድ አገራት ከተሸረበባት ተንኮል ስር ሳይሰድ አርነት የሚያወጣ አንድ እንቅስቃሴ በእንጭጩ ተጨናግፎ ቀረ። (በነገራችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሳስብ ሁሌም የሚቆጨኝ ይህ የታሪክ ምዕራፍ ነው! አዳዲስ ባዕድ ሀይማኖት ሲመጡ ለመቀበል የማይቸግረው ህዝብና አገር ከውስጡ የወጡ የለውጥ አራማጆችን መቻልና ማድመጥ ተስኖት የራሱን ወገን ያውም (የእግዚአብሔር ሰው ነኝ የሚል) እንዲህ ሲሰለቅጥ በታሪካችን የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም። ንጉሱ ደግሞ የለውጥ ሀይሉን ከበላ ብኋላ፣ ጭራሽ ከለውጥ ሀይሉ በተቃራኒ የሆነ ነገር በአዋጅ እንዲፀድቅ አደረገ! )


በዚህ ባለንበት ዘመን ሳይንስና ምክንያታዊነት ጣራ በነካበት ዘመንና ተፅእኖዎቹ በተጨባጭ ጎልተው በሚታዩበት ዘመንም፣ እንቅፋትና ለውጥ አጨናጋፊ አድሀርያን በየቦታው አሉ። የአየር ለውጥ መዛባት ውሸት ነው የሚሉ፣ ግሎባል ዋርሚንግ ቢኖርም ሰው ሰራሽ አይደለም የሚሉ፣ የበርሃማነት መስፋፋት ተረት ነው የሚሉ (ከአንድ አስተማሪዬ ጋር የተጋጨሁበት ወቅት ነበር በዚህ ጉዳይ!) በዚህ በሰለጠነው የዓለማችን ክፍልም አሉ። ክትባት የሚፈሩ ብቻ ሳይሆን ህዝብን በተቃራኒ የሚቀሰቅሱ፣ የተዳቀሉ የሰብልና የእንስሳት ምርቶች ሰው እንዳይበላ የሚቀሰቅሱ፣ የተሳሳተ ትምህርት የሚያስተምሩ፣ ወዘተ በየቦታው አሉ። ከዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ጀርባ ያሉ ሰዎች ቢጠኑ መነሻ ምክንያታቸው ከሁለት ነገሮች አይዘሉም፥ አንድም በሳይንስ ምክንያት የሚጎድልባቸው ጥቅም ይኖራል አሊያም አለማወቃቸውን የማያውቁ አዋቂ ነን ባይ ግብዞች (በጨዋ ቋንቋ – ደንቆሮዎች!) ይሆናሉ። በተለያየ ዘርፍ የህዝብን ኑሮ በማሻሻል ረገድ፣ የሰው ልጅ በህይወት የሚኖርበት አማካኝ ዕድሜን ከፍ በማድረግ ረገድ፣ እወቀትና መረጃ ሁሉም ዘንድ የሚደርስበት መንገድ በመጥረግ ረገድ፣ . . . በአጭሩ ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ከነበረው የሰው ልጅ ኑሮ በማንኛውም መመዘኛ በብዙ እጥፍ የተሻለ ህይወት እንድንኖር ያስቻለን (ለዘላለም ይንገስና!) ሳይንስ ነው። ይህ ሲባል ግን ሳይንስ ህዝብ ላይ ያስከተለው ምንም ዓይነት ችግር የለም ማለት አይደለም። ሁሌም የሳይንስ ዓላማ በጎ ቢሆንም አልፎ አልፎ ይሳሳታል። የስህተቱ ገፈት ቀማሾች ይኖራሉ። ከዛ የከፋው ግን ሳይንስ ልክ እንደጠላቶቹ ሁሉ ለክፋት የሚጠቀሙበት “ወዳጆችም” አሉት።

ለምሳሌ አንዳንድ ሳይንሳዊ ግኝቶች ለጦርነት ሲውሉ ይታያል። እንደዚህውም ዘረኛ ፖሊሲ ለሚያራምዱ ሳይኮፓዝ መሪዎች ጥሩ ዘረኝነትን የማስፋፊያ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ። ዛሬ በአገራችን እየተከናወኑ ካሉ አስፀያፊ ምግባሮች መካከል ሌላ ምሳሌ እንመልከት ቢባል የዘመኑ አወናባጅ ነብያትና ደብተራዎችን ማየት ይቻላል። እነ ነብይ እስራኤል ዳንሳና መምህር ግርማ ሲታመሙ ሌላ ነብይ ወይም መምህር ዘንድ አይሄዱም። የሚሄዱት ውጭ ድረስ ዘመናዊ ህክምና ለመታከም ነው (መፅሀፍ ቅዱስ ጨብጦ ድራማ በመስራት እድናለሁ ብለው ሲሞክሩ አታዩም!) ። የሀብትና የዝና ምንጫቸው የሆነውን ድሃው በቀጥታ እነሱ ዘንድ እንዲሔድ የሚያጠምዱት የሳይንስ ውጤቶችን በመጠቀም ነው። የውሸት ትርክታቸውን ለበርካታ የዋህ ምእመኖቻቸው የሚያደርስላቸው የዘመኑ ቴክኖሎጂ (ካሜራው፣ መብራቱ፣ ድምፅ መቅረጫው፣ ማህበራዊ ሚድያው ምኑ) የሳይንስ ውጤት ነው። ዝናና ገቢያቸው እንደዚህውም ተፅእኗቸው እየገነነ የሚሔደውም በነዚህ የሳይንስ ውጤቶች አማካኝነት ነው። ሁሉንም ለመጥቀም የተፈጠረው ቴክኖሎጂ ለአጭበርባሪዎች ሲሳይ ለሌሎች የባርነትና የብዝበዛ ቁስ ሲሆን እንደማየት የሚያም ነገር ፈፅሞ የለም።

ቢሆንም ጥቅምና ጉዳቱ ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለምና፣ ከጠላቶቹ ይልቅ ወዳጆቹ እንደ አሸን የፈሉ ናቸውና ሳይንስን እናፈቅረዋለን። እንገለገልበታለን። ቀርበን እናጠናዋለን። እንከታተለዋለን።


Re: የፍልስፍና እና የሳይንስ ወጎች – ካነበብኩት

Posted: Tue Oct 07, 2025 1:03 pm
by yaman

ከወለድ ነጻ የሆነ የባንክ አሰራር አለ?

ክርስትናና እስልምና ከነመፈጠራቸው ሳይታወቅ በፊት፣ አራጣ ጽያፍ ነበር። የግሪክ ፈላስፋዎች እነ ፕላቶና አሪስቶትል ጽፈውበታል። አራጣ ሞራሊ ትክክል አይደለም የሚል ውግዘት ከዛን ግዜ ጀምሮ ነበር።

ኢንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል፣ History of Western Philosophy በሚለው ገናና ስራው እነዚህን ፈላስፋዎች በጥልቀት ይተቻል። ሎጂካል አይደለም ይላል። ኢንተግሪቲያቸውንም ጥያቄ ውስጥ ይከታል። እንደ ራስል አገላለጽ አበዳሪና ተበዳሪ ከጥንት ጀምሮ ነበሩ። አበዳሪዎች አራጣ ይፈልጋሉ፣ ተበዳሪዎች አራጣ አይፈልጉም። በዛን ዘመን ተበደሪ የመሬት ከበርቴው ሲሆን አበዳሪው ነጋዴ ነበር። የፖለቲካ ስልጣን የነበራቸው ደግሞ የመሬት ከበርቴዎቹ ነበሩ። የያኔ ፈላስፋዎች አንዳንዶቹ መደባቸው/ክላሳቸው ከከበርቴዎቹ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ የከበርቴዎቹ ቅጥረኞች ነበሩ። እናም አራጣን ሲኮንኑ ለተበዳሪ ከበርቴ የሚያደላ ህግ ማስቀመጣቸው ነበር።

ከግሪክ ፈላስፋዎች ብኋላ የመጡት የቤተክርስትያን ፈላስፋዎች (እነ St. Augustine እና St. Thomas Aquinas) ነበሩ። ያኔም ቤተክርስትያን የመሬት ከበርቴ ነበረች። እናም ቄሶቹ ፈላስፋዎች አራጣ ውጉዝ ነው የሚለውን የቆየ የግሪክ ፍልስፍና መቀየር አላስፈለጋቸውም። ተቀብለው ቀጠሉበት። በተለይ ደግሞ ያኔ አበዳሪዎች የነበሩት ጅዊሽ ነጋዴዎች ስልሆኑ፣የአራጣን ውጉዝነቱን በደንብ አጸኑት። … ይላል ፈላስፋው ራስል።

ከክርስትና ብኋላ እስልምና ተከለተለ። መቼስ መጽሀፍቱ ብዙም ልዩነት የላቸውም። እስልምናም ላይ አራጣ ሃራም ሆኖ ቀጠለ። አስር እጥፍም ቢሆን ነግዶ ማትረፍን ይፈቅዳል፣ ሰባራ ሳንቲም በአራጣ መክፈል ወይም መቀበል ይኮንናል። ብኋላ በዝርዝር እንደምናየው በዘመናዊ የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ትርፍም ሆነ ወለድ ለከት አለው። አንድም በገበያው አሊያም በህግ የተገደበ ተመጣጣኝ ትርፍና ወለድ ብቻ ነው የሚፈቀደው።

አንድ ምሳሌ እንመልከት። ዛሬ በአንድ ብር ዳቦ ገዝተህ ነገ በ5 ብር መሸጥ ትችላለህ፣ እስልምናም ክርስትናም እዚህ ላይ ችግር የለባቸውም። ነገር ግን ዛሬ ለአንድ የተቸገር 1 ብር አበድረህ ነገ 5 ብር መቀበል ውጉዝ ነው። ምናልባት ለልጁ የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለውና ልጁን በህይወት ለማቆየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ዛሬ 1 ብር ካንተ ተበድሮ ዳቦ በመግዛት ነገ ደሞዙን ሲቀበል 5 ብር ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነው። በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት የዳቦ እጥረት ስላለና ልጁን በህይወት ለማቆየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ትላንት በብር የገዛኸውን ዳቦ ዛሬ በ5 ብር እንድትሸጥለት የሚጠይቅህ። ግድየለም ትላንት 1 ብር ነው የገዛሁት፣ በብር ከአምሳ ውሰደው፣ ተገቢ ያልሆነ ትርፍ መሰብሰብ የለብኝም ሀራም ነው ወይም ሀጥያት ነው የሚል አማኝ በባትሪ ፈልጋችሁም ላታገኙ ትችላላችሁ። ነገር ግን ሁለቱ ሴናሪዮዎች ፋንዳሜንታሊ ተመሳሳይ ናቸው፣ ልዩነታቸው ቴክኒካል ነው።

በኢኮኖሚክስ ገንዘቡን ራሱ እንደ አንድ ኮሞዲቲ (ልክ እንደ ዳቦው) እናየዋለን። ዛሬ አንድ ብር ዋጋው አንድ ብር ነው። ከአመት ብኋላ ዋጋው ብር ከስሙኒ ሊሆን ይችላል። የምትገዛው ወረቀቱን ሳይሆን የገንዘቡን ቫልዩ ነው። ዳቦው ዛሬ አንድ ብር የነበረው ነገ 5 ብር የሚሆነው ቫልዩው ነው። እንጂ ዳቦነቱ አልተቀየረም። ያውም ሲቆይ ይሻግታል ወይም ኳሊቲው ይቀንሳል። ነገር ግን በምንገዛበት ሰዓት በጣም ስለፈለግነው የሆነ ቫልዩ ዳቦው ላይ አታች አድርገናል፣ ለዛ ቫልዩ ነው ተጨማሪ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የምንሆነው። ሰውዬው ልጁን ካላበላ የከፋ ኪሳራ ሊገጥመው ስለሚችል 5 እጥፍ ከፍሎ መግዛት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ታይቶቷል። አንተም የ4 ብር ትርፍ ካገኘህ፣ ቀን እንደወጣልህ ቆጥረክሀው እየቦረቅክ ወደ ቤትህ ትሔዳለህ። ያ ሰው በ5 ብር የገዛህ ተቸግሮም ቢሆን ስለሚችልና የባሰ ኪሳራን ማስቀረት ስለሚፈልግ ነው። 1ን ብር በ5 ብር ነገ ለመቀየር የሚስማማህም ስለሚችልና ስለነገ የተሻለ ኤክስፔክቴሽን ሳለለው ነው። ካልቻለና ተስፋው ከተሟጠጠ ግን ስርቆትና ዘረፋ ውስጥ ነው የሚገባው። (እንኳን ወለድ ሌብነትም ጀስቲፋያብል የሚሆንበት ግዜና ሁኔታ አለ!)

ወደ ታሪኩ እንመለስ። ከእስልምና ብኋላ የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን መጣ። አብዛኛዎቹ ፕሮቴስንታንቶች ነጋዴዎችና የተማሩ ደሞዝተኞች ነበሩ። ነጋዴ ወለድ ይፈልጋል። ደሞዝተኛም ወለድ ይፈልጋል። ወለድ መሰብሰብና መክፈል ምንም ክፋት አላዩበትም። የነዚህ መደብ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስታተስ ላይ ነበር። ህጉ እንዲቀየር ጫና ፈጠሩ፣ ሪፎርም ተደረገ። ሪዝናብል የሆነ መጠን እስከሆነ ድረስ interesse (or late payment) መክፈል ችግር የለበትም ተባለ። የካቶሊክ ቤተክርስትያን ለውጡን ተቀብላ ተራመደች። የተጋነነ ወለድ እንዳይጠየቅ ወዘተ ማሻሻያ ህጎች እየወጡ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ቃሉም interest ወደሚለው ቃል ኢቮልቭ አደረገ። ክርስትያኖች ዛሬ የባንክ ወለድ ሲባል ምንም የማይመስላቸው አንድም ምክንያቱ ይኸው ነው። በአራጣና በወለድ መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘባሉ።

ዘመናዊ ባንክ እውን ከሆነበት ዘመን አንስቶ ያለወለድ የሚሰራ ባንክ የለም! ልዩነቱ አንዳንዶች በግልጽ የሚቀበሉትና የሚከፍሉት የወለድ መጠን ሲያሳውቁ፣ ሌሎች እንኳን ሊያሳውቁ ወለድ የሚለውን ቃል ከነአካቴው አይጠቅሱም። አሜሪካ ውስጥ ሞርጌጅ የሚያበድሩ አንዳንድ ባንኮ interest free እና with interest rate የሚሉ ቅጾች አሏቸው። የቤቱ ዋጋና ወርሃዊ ክፍያው ሁለቱም ላይ እኩል ነው። አንደኛው ለሙስሊሞች ሌላኛው ደግሞ ለሌሎች የተዘጋጀ ቅጽ ነው። ሌሎች ባንኮች ደግሞ አሉ ጭራሽ ከወለድ ነጻ ነን የሚል ነጭ ውሸት ይጨምሩበታል። እርግጥ ነው የቁጠባ ገንዘብ ሲቀበሉ ከወለድ ነጻ ነው፣ የሚከፍሉት ነገር የለም። ሲያበደሩ ግን ወለድን ታሳቢ አድርገው ነው ወርሓዊም ይሁን አመታዊ ክፍያ የሚሰበስቡት።

አራጣ (usury) እኛም አገር እስከ ቅርብ ግዜ ነበረ። ምናልባት አሁንም ድረስ ገጠር አካባቢ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ህገወጥ ነው። በእምነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በመንግስት ህግም የተወገዘ ነው። መንግስት አራጣ አበዳሪን እያሳደደ ያስራል፣ ሀብቱን ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ያደርጋል። ልክ እንደ አራጣው ሁሉ፣ በህግ የተደነገጉ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ዘርፎችና እንቅስቃሴዎች አሉ። ለምሳሌ ትርፍን ለማጋበስ በመሻት አርቴፊሻል እጥረት ፈጥረው (ሆርዲንግ ይባላል) ዋጋ እንዲወደድ የሚያሴሩ ነጋዴዎች የትም አገር በህግ ይጠየቃሉ። በሞኖፖል የሚያመርቱት ምርት ወይም የሚሰጡት አገልግሎት ላይ የፈለጉትን ዋጋ መተመንና ትርፍ ማጋበስ አይችሉም። አንቲ ትረስት የሚባል ህግና ተቋማዊ አሰራር አለ። እኛም ጋ አንድ ሰሞን ሲያስመርሩት መለስ ዜናዊ ነጋዴዎችን ማሳደድ ጀምሮ ነበር። የዋጋ ተመን ሁሉ ማስቀመጥ ጀምሮ ነበር። እዛ ንግድ ውስጥ ሙስሊሞች ነበሩ፣ ወለድ ሓራም ነው የሚሉ። ነገር ግን ወለድ ከሚጠይቀው በላይ ድሆችን ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመጨመር ሲበዘብዙ የነበሩ ሱቃቸው የተዘጋባቸው ሙስሊም ነጋዴዎች ነበሩ። ክርስቲያኖችም ነበሩ ፎር ዛት ማተር። መልካቸውን ቀይረው በባንክ ድሪቶ ተጀቡነው መምጣታቸውን እረዳለሁ አሁን።

ይህን ሁሉ የማወራው፣ ከመነሻው፣ ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምራችሁ ሁኔታውን በደንብ እንድትረዱና እንድትጠይቁ ነው። ወለድ በግልጽ መሰብሰብ ችግር የለበትም። የግድም ነው። ከሌላ የቁስ ዋጋ ጋር ለማመጣጠንና የመግዛት አቅሙን ለማካካስ የግድ ወለድ መኖር አለበት። ሰዉ ያለው አማራጭ መረጃውን አገናዝቦ የሚያዋጣውን መወሰን ነው። አበዳሪ (ሴቭ አድራጊ) ከሆነ ከፍተኛ ወለድ የሚሰጡትን፣ ተበዳሪ ከሆነ ደግሞ ዝቅተኛ ወለድ የሚጠይቁትን መርጦ ቢዝነሱን ማፋጠን። ወለድ ከመክፈልና ከመሰብሰብ የከፋ ብዙ ቆሻሻ ስራዎች ይሰራሉ። ከነዚህ መካከል ይህ ከወለድ ነጻ ነኝ የሚል የቀፍለህ ብላ ቢዝነስ ይገኝበታል። እርግጥ ነው በየቀኑ ባንክ የሚዘረፍበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። ቢያንስ ግን እነዚህ ዘራፊዎች ወንጀለኞች መሆናቸውን የሚጠራጠር የለም። መረጃን በመደብቅና የሚያወሩትና የሚሰሩት በማወናበድ፣ የሰው ሀብት የሚዘርፉ፣ ሰው የሚገባውን እንዳያገኝ የሚያሴሩ ከባንክ ሰባሪዎቹ የከፉ ወንጀለኞች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል።


Re: የፍልስፍና እና የሳይንስ ወጎች – ካነበብኩት

Posted: Tue Oct 07, 2025 1:15 pm
by yaman

ሃቅ ሃቁን ብቻ እናውራ ከተባለማ፣ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ፍልስፍና እይታቸውን ፈጽሞ የማልስማማበት፣ ነገር ግን በጣም የማደንቃቸው ባለ ከባድ ሚዛን አስተማሪዎቼ (ተጽእኖ ፈጣሪዎች) በምድር ላይ ሁለት ሰዎች አሉ/ነበሩ። መለስ ዜናዊ እና አያን ራንድ። የአትላስ ሽራግድ እና ዘ ፋውንቴን ሄድ ደራሲዋና ፈላስፋዋ ራንድ፣ በጆን ጋልት እና በሃዋርድ ሮርክ አማካኝነት የምታስተላልፋቸው፣ ፍጹም የማታወላዳበት የኦብጀክቲቪዝም ፍልስፍና ብላ የምትጠራው ግለሰባዊነትን እስከጥግ ድረስ ለጥጣ የምታወድስባቸው ስራዎቿ በብዙ የማልስማማባቸው (አንዳንዴ የምጸየፋቸው ጭምር) ቢሆንም፣ ብዙ የተማርኩባት እና የማደንቃት ጸሃፊ ናት። ስለ ራንድ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። አሁን ስለ መለስ እናውራ።

ራሳችንን ካልዋሸን በስተቀር፣ መለስ በተለይ በኢኮኖሚክስ ትንተናው አንድን ትውልድ አነሳስቷል፣ ቀርጿል፣ ቢባል ማጋነን አይሆንም። በመለስ ዘመን ስለ ዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ የማይደሰኩር ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ ተማሪ፣ ካድሬ ወዘተ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስለ ኢኮኖሚክ ፓራዳይም፣ ስለ ግሪን ኢኮኖሚ፣ ስለ ኒዮሊበራሊዝም፣ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት (ሬንት ሲከርስ) ወዘተ የማይወራበት፣ የማይተነተንበት እና የማይተችበት ቀን አልነበረም። በፖለቲካው ልንቃወመውና ልንጠላው እንችላለን (በዛም ረገድ ሻምፕዮን እንደነበር አሁን እየበራልን ቢሆንም)፣ በኢኮኖሚክስ እውቀቱ፣ የትንታኔ ብቃቱ፣ ከኢንግሊዝኛ ወደ አማርኛና ትግርኛ የመመለስ ብቃቱ ግን ማንም ሰው አይክደውም።

እስኪ እውነት እንናገር እና፣ ስለ ርዕዮተ አለም፣ ስለ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ፣ ስለ ኢኮኖሚክ ፍልስፍና ከመለስ ዘመን ወዲህ በማህበራዊም በሉት በመንግስት ሚድያ ተወርቶ ያውቃል? ያ አጀንዳ፣ ያ ሙግት፣ ያ ትችት አልናፈቃችሁም? በነ ኮንፍዩዝድ እና ኮንቪንስ ዘመን፣ መደመር ከምትለው የ3ኛ ክፍል አርቲሜቲካ የዘለለ አንዲት ቃል ሳንሰማ አስር አመት ሊሞላን ደረሰ። በመለስ ዘመን ፎር ግራንትድ ወስደነው የነበረ ጸጥታ፣ የማዕከላዊ መንግስት ጥንካሬ፣ ወዘተ ከመለስ ወዲህ አፈርድሜ ግጦ፣ ወሬያችን እና ኑሯችን ሁሉ ስለ ጦርነት ብቻ አልሆነም? እንደ ዘመነ ደርግ፣ ብልጽግና እድሜዋን በጦርነት ፈጀችው። ቅቤው ኢንስፓየር ያደረገው ትውልድ ቢኖር እነ ምናምን ድሪምስ እንደሚባሉት አነቃቂ እና ሰባኪ ነን ባዮችን ብቻ ነው። (የበርትራንድ ራስል ፍልስፍና መጽሃፍ ካነበባችሁ፣ እንዲህ አይነት ሰዎች የሚበራከተቱ ከአንድ ማህበረሰብ ውድቀት እና ስብራት ብኋላ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። ትኩረት ሁሉ ራስን ለማጽናናት፣ ቀኑን እንደምንም ለማሳለፍ ይሆናል። የስቶይሲዝም ፍልስፍናን በዚህ መልኩ ነው ሩስል የሚገልጸው። ግሪኮች በጦርነት ተሸንፈው አገራቸው እንክትክት ስትል እና በሌሎች ቁጥጥር ስር ስትወድቅ፣ ያ ሰማይ ምድሩን የቧጠጠው፣ ከአተም እስከ አጽናፈ አለም የቃኘው ፍልስፍናቸው ከስሞ በነ ኢፒኲሬስና ኢፒክቲቱስ የሃፒነስ ፍልስፍና ተተካ። አይንህን ጨፍነህ የልብ ትርታህን ካዳመጥክ፣ ጭንቀትህ ሁሉ ውልቅ ብሎ ሲሔድ ታያለህ። የደስታ ምንጭ ወደ ውስጥ መመልከት ነው። ወዘተ)

መለስ በአደባባይ ጭምር ደረቱን ነፍቶ እየተከራከረ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከኒዮሊበራላይዝም ታደገው። በየጊዜው የሚቀርብበትን ጫና ተቋቁሞ፣ ተከራክሮ፣ እነ ጆ ስቲግልቲዝ አስደምሞ፣ የኢኮኖሚ ሉኣላዊነቱን አስከብሮ አለፈ። (አገሪቱ በየጊዜው የምትቀበለውን ምጽዋት ወደጎን ብለን)። ዛሬ አንድም ሳይቀር ገበያው በሙሉ ተበርግዶ ላለው ሲሰጥ፣ አንዲትም ክርክር አልተደረገም፣ ወይ አመክንዮ አልቀረብም። እንደሾካካ የተባለቱን ፈጽመው ጭጭ አሉ። ሃሳብ የደረቀበት ስርዓት እና ዘመን ላይ ሆነህ እንደ ወ/ሮ ጊዜሽወርቅ ተሰማ *የGize plc መስራች እና CEO) በድፍረት ምስክርነትህን ስትሰጥ ... ያምርብሃልና የኔን እንሆ አልኳችሁ።