የዶላርና የብር ወግ – ጥቂት ነጥቦች ስለ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ

በክቡር ገና

For the English version click here

የዶላር ተመን | Currency

ስለ ውጪ ምንዛሪ ዋጋ ተመነ ቅነሳ ከመግባቴ በፊት ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ካለውና የሰሞኑ ዋናና አንገብጋቢ ከሆነው ኢትዮጵያ የውጭ ብድሯን መክፈል ያለመቻሏን ጉዳይ በጥቂቱ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢና አደገኛም ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ብድርን መክፈል ያለመቻል አበዳሪውን ብቻ ሳይሆን ተበዳሪውንም የሚጎዳና በቀጣይነትም ጉዳዩ ብዙ መዘዝ ይዞ ስለሚመጣ ነው፡፡

አንዲት ሀገር ብድር መክፈል ሲሳናት ተከትሎ የሚመጣው ጣጣ የትየለሌ ነው፡፡ አንዲት ሀገር ብድር መክፈል ሲያቅታት በመጀመሪያ አበዳሪዎች በእርግጠኝነት ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከብድር ጋር በተገናኘ ስራቸውን የሚያከናውኑ የብድር አማካሪዎች፣ የህግ ጉዳዮች አስፈጻሚዎችና በብድር አፈጻጸም ሂደት ውስጥ ተዋንያን የሆኑ አካላት በሙሉ ተጎጂዎች ይሆናሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ዜጎች ይጎዳሉ፡፡ ሀገራት ብድራቸውን መክፈል ሲሳናቸው ቀጣይ የሚበደሩት ብድር ወጪው ይንራል (ለዚያውም የሚያበድራቸው ከተገኘ)፡፡ ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉ ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ስለሚሸሻቸው ኢኮኖሚያቸው ተዳክሞ ውጤቱ በአሉታዊ መልኩ ለዜጎች ይተርፋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዲት ሀገር ‹‹ ብድሯን መክፈል የተሳናት›› የሚለው ክፉ ስም በአለም አቀፍ ገበያ የሀገርን ዝናን የሚያጎድፍ ከመሆኑም በላይ ለተከታታይ አመታት በአለም አቀፍ የፋይናነስ አፈጻጸም ተሳትፎ እምነትን የሚያሳጣና መጥፎ ጥላ እንዲያጠላባት የሚያደርግ ነው፡፡


ተመሳሳይ ርዕሰ ለማንበብ > ከምጽአተ-ኢትዮጵያ እንተርፍ ይሆን? በልደቱ አያሌው


ኢትዮጵያን ለዚህ ፈታኝ ሁኔታ ከዳረጓት ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋንኛው በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ግጭትና የሰላም እጦት ነው፡፡ በሀገሪቱ እዚህም እዚያም የተከሰቱት ተከታይ ግጭቶች የሀገሪቱን እድገት አቀጭጨዋል፣ የወጪ ንግድን አዳክመዋል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተዳከመ ኢኮኖሚ የገቢ ንግዱ ጨምሯል በተለይም ለጦር መሳሪያ ግዚ የሚወጣው ወጪ ንሯል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካና የምራባውያን ስትራቴጂያዊ አጋር የነበረችው ኢትዮጵያ በአመራር ጥበብና በዲፕሎማሲው ዘርፍ በታየው ድክመት ሚናዋን ለኬኒያ አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ ተጽዕኖ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ታገኝ የነበረው ድጋፍና ትብብር ክፉኛ ተመናምኗል፡፡

ይህን የውጭ ብድርን መክፈል ያለቻል ጉዳይ በሌላ ወቅት እመለሰበታሉ፡፡ አሁን ወደ ተነሳሁበት የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ቅኝት ልግባ፡፡

በዚህ አመት ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ለማድረግ የተዘጋጀች ይመስላል፡፡ በዚህም ዶላር በብር የሚመነዘርበት የዋጋ ተመን አሁን ካለበት ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የሰሞኑ መደበኛ የዶላር የውጭ ምንዛሪ ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ56 የኢትዮጵያ ብር የሚመነዘር ሲሆን ኢትዮጵያ እንዳሰበችው የውጭ ምነዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ የምታደርግ ከሆነ አንድ የአሜሪካ ዶላር አሁን በህጋዊው ምንዛሪ ካለው 56 ብር እንደሚጨምር ይገመታል፡፡

ዶላር በብር የሚመነዘርበት መጠን ጨመረ ማለት የብር የዋጋ ተመን ቀነሰ ማለት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ተመን ዋጋ ቅነሳ ለማድረግ ሽር ጉድ እየተባለ ያለው ከአለም ባንክና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጀት እርዳታና ብድር ለማግኘት አንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ አለም አቀፍ ተቋማት ለአንድ ሀገር ድጋፍ የሚያደርጉት በቅድመ ሁኔታ ስለሆነ ድጋፉን ለማግኘት ሀገሮች የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ አስገዳጅ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚገደዱ የተቋማቱ የቀድሞና የአሁን ታሪክ ያመለክታል፡፡

በአንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ሲደረግ በአብዛኛው የሚከተሉት አብይ ጉዳዮች መከሰታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ሲካሄድ ወዲያውኑም ሆነ ዘግይቶ ችግሮቹ ይመጣሉ፡፡

1. የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ የአንድን ሀገር ሀብት ያመነምናል

የአለም ታሪክ እንደሚያሳው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ በተደረገባቸው አገሮች ጥቂት ቡድኖች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን ከውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳው ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ወደ ድህነት ለመንደርድር ጉዞ ይጀምራል፡፡

2. ሀብታሞች ሀብታቸውን ወደ ውጭ እንዲያሸሹ ያደርጋል

በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ምክንያት የሚፈጠረውን ኪሳራ ለማምለጥ ሀብታሞች ሀብትና ገንዘባቸውን በሌሎች ሀገሮች ገንዘቦች በመቀየር ወይም በውጭ ሀገር ንብረት በማፍራት ሀብታቸውን ከኪሳራ ለመታደግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ተራው ህዘብ ወይም ድሀው ዜጋ ግን ይህን ማድረግ ስለማይችል የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳው ገፈት ቀማሽ ይሆናል፡፡
ሀብታሞች ገና የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ እንደሚደረግ ጭምጭምታ ሲሰሙ ሀብታቸውን ወደ ውጭ ሀገር አንደሚያሸሹ ይታወቃል፡፡ ሀብታሞች ከተራው ህዝብ በተሸለ ሁኔታ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መረጃ ስላላቸው አሰከ አሁንም በርካታ ሀብት ወደ ውጭ እንዳሸሹ ይገመታል፡፡
የሀብታሞቹ ጉዳይ ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሸ ብቻ አያበቃም፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም ሲዳከም ሀብታሞች ወደ ሀገር በመመለስ ባሸሹት ሀብት በሀገር ወስጥ በመነገድና ኢንቨስት በማድረግ ንብረቶችን እሳት በሆነ ዋጋ ለዜጎች ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የሪል ስቴት ገበያ ነው፡፡

3. የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛንን ያዛባል

እንደማንኛውም ታዳጊ ሀገር ኢትዮጵያ ከውጭ በምታስገባውና ወደ ውጭ በምትልከው ምርት መካከል ትልቅ የንግድ ሚዛን መዛባት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ሸቀጦች ለማምረት ግብአቶችን ከውጭ ታስገባለች፡፡ ለምሳሌ አንድን የግብርና ምርት ለማምረት የአፈር ማዳበሪያ፣ የተለያዩ ግብርና መሳሪያዎች፣ ኬሚካሎችና ሌሎች ግአቶችን ከውጭ ታስገባለች፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማምረትም ለኢንዱስተሪ ምርት የሚሆኑ ግብአቶች በአብዛኛው ከውጭ ነው የሚመጡት፡፡

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ በተደረገበትና የዶላር ዋጋ ከፍ ብሎ የብር ዋጋ ዝቅ ባለበት ሁኔታ እንደ ልብ ዶላር ተገኝቶ ለምርት ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን ከውጭ አምጥቶ ምርቶችን በገፍ ወደ ውጭ መላክ ስለሚያዳግት የወጪ ንግዱ መዳከሙ ግልጽ ነው፡፡
ስለዚህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ተግባራዊ ሲደረግ በሀገር ወስጥ የማምረቻ ወጪ ይጨምራል፡፡ ይህም በተራው የሀገር ውስጥ ምረት እድገት እነዲቀነጭር ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ቀድሞ የነበረውን የወጪና ገቢ ንግድ አለመመጣጠንን ይበልጥ በማዛባት እንደ ፊኛ እንዲያብጥ ያደርገዋል፡፡

4. ዜጎችን ይበልጥ ያደኧያል

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ተግባራዊ ሲደረግ ዜጎችን በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በሶስት አይነት መንገድ ይጎዳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ገቢ ይቀንሳል፣ ስራ አጥነጥትን ያስፋፋል እንዲሁም መንግስት ለድሀ ዜጎች የሚያቀርበውን አገልግሎት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ሲቀንስ ደሞዝተኛ የሆኑ ዜጎች እውነተኛ ገቢ ይቀንሳል፡፡ መንግስት በትምህረት፣ በጤና፣ በምግብ ሸቀጥ ድጎማና በመሳሰሉት ማህበራዊ ከለላ ለዜጎች የሚያቀርበው አገልግሎት ስለሚቀንስ ድሆች ይበልጥ ድሀ ይሆናሉ፡፡

5. የመንግስት ወጪ እንዲጨምር ያደርጋል

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ የገቢ ንግድ ወጪዎችንና የእዳ ክፍያዎችን በማናር የመንገስት ወጪ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ መንግስት ወጨዎቹን ለመሸፈንና የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ሲል በገቢ አሰባሰብ ረገድ ከፍተኛ ጭማሪ ሊያደርግ ይገደዳል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ ውስብስብ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ የመንግስትን ገቢ እንዲጨምር የሚያደርግበትም እድል አለ፡፡ በተለይም በንግድ ስራዎችና በተለያየዩ ገቢዎች ላይ ከፍተኛ ግብር በመጣል የመንግስት ገቢ እንዲጨምር ማድረግ ይችላል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ጋር በተያያዘ ከመንግስት የልማት ድረጅቶች የሚያገኘው ትርፍም ሊጨምር ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የገቢ ጭማሪ ከወጪው ጋር ሲነጻጸር ስለማይመጣጠንና ውጤቱም ወዲያውኑ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

6. ለውጭ ሀይሎች ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት ያጋልጣል

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባቸው በርካታ ሀገራት የዕዳ ክፍያ እፎይታ፣ ብድርና እርዳታ ለማግኘት የአለም አቀፍ ተቋማትን ድጋፍ ይጠይቃሉ፡፡ እንደ አለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት ያሉ አለም አቀፍ ተቋማት የተጠየቁትን ድጋፍ ለመስጠት መንግስታትን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ እንዲያደርጉና ሌሎች አስገዳጅ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ተጽዕኖ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ውጤታማነት በወጪ ንግድ እድገት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሆኖም ግን የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ቀድሞውኑ በተዛባበት፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ዋጋቸው በጨመረበትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ባልተቻለበት ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ማድረግ ብቻውን የወጪ ንግድ እድገትን አያመጣም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን፣ የማምረቻ ማሺነሪዎችን፣ መለዋወጫዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን ከውጭ ማስመጣትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ማደረግ በገቢና ወጪ ንግድ መካከል የነበረውን የንግድ ሚዛን ይብሱኑ የሚያዛባው ሲሆን በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ምንያት ይመጣል የተባለው የወጪ ንግድ እድገት አዝጋሚ ሆኖ የገቢ ንግዱ እድገት ግን ወዲያውኑ የሚከሰት ይሆናል፡፡

ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ተደርጎ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚገኘው ገንዘብ ብድር እንጂ እርዳታ ወይም ችሮታ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ ብድር ደግሞ ወለድ አለው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ አድረገን የምናገኘው የእዳ ክፍያ ሽግሽግም የአገልግሎት ክፍያ አለው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ማድጋችን ከወለድና ከእዳ ሽግሽግ የአገልግሎት ክፍያ አያድነንም፡፡

እናም የሀገሪቱ ገቢ ለወልድና ለእዳ ሽግሽግ የአገልግሎት ክፍያ ስለሚውል ለልማት ፕሮጀjክቶች ግንባታና ኢንቨስትመንት የምናውለው ሀብት አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በድህነት አርነቋ ውስጥ ስንዳክር እንድንኖር ከማድረጉም በላይ እኛ መክፈል ያቃተንን የእዳ ጫና ለልጆቻችን እንድናወርስ ልንገደድና የማንወጣው አዙሪት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡

ከዚህ አዙሪት ተጠቃሚዎች እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና አጋሮቻቸው ያሉ ድንበር ዘለል አለም አቀፍ ተቋማት ሲሆኑ በአሁኑ ዘመን ይበልጥ ትርፋማው ስራ ምርና አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ ሳይሆን አበዳሪ መሆን ግንባር ቀደም አትራፊ ስራ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

7. የዋጋ ንረትን ያባብሳል

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተከናወኑ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳዎች የዋጋ ንረትን በማስከተል ኑሮን እሳት አድረገዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ምንያት የተከሰተው የዋጋ ንረት በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ጭምር ተስተውሏል፡፡ የዋጋ ንረት ከማስከተሉም በተጨማሪ የወጪ ንግዱ እንዲቀጭጭና የገቢ ንግዱ ደግሞ እንዲስፋፋ ነው ያደረገው፡፡ እናም ለመጨረሻ ጊዜ በኢትጵያ የተካሄደውን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ስንመለከተ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አወንታዊ ሚና አልነበረውም፡፡

8. ድንገተኛ የኑሮ ምስቀልቅል ይፈጥራል

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ አሉታዊ ገጽታ ውጤቱ ቅጽበታዊ መሆኑ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ በተደረገ ማግስት ድንገተኛ የኑሮ ምስቅልቅል ይፈጠራል፡፡ አንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ስታደርግ በአለም አቀፍ ደርጃ የምትገዛቸውና የምትሸጣቸው ምርቶች ዋጋ የጨምራል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገዙ ሸቀጦች ወዲያው ዋጋቸው ይጨምራል፡፡ የእውነት እንነጋጋር ከተባለ የብር መግዛት አቅም ሲቀንስ ዘርፈ ብዙ የኑሮ ምስቅልቅቅ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ እስቲ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ካደረግን በኋላ ወደ ሀገር የምናስገባውን የነዳጅ ዋጋ እናስበው? ዋጋው እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኛ ሀገር ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የማጨምር ምርትና አገልግሎት የለም፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ የኑሮ ምስቅልቅል ወደ እያንዳዳችን ቤት ሰተትብሎ ገባ ማለትም አይደል?

በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳው የኛ ኑሮ በዚህ መልኩ ሲመሰቃቀል በአለም ገበያ ሸቀጣቸውን ለሚሸጡ ወገኖች ግን ተጨማሪ ትርፍ እንዲዝቁ ያስችላቸውል፡፡ በተለመደውና ተፈጥሯዊም መንገድ ምርት አምርተው ወደ ውጭ ለሚልኩ አዳዳስ ካምፓኒዎች ግን ትግሉ ፈታኝ ነው፡፡ ሁኔታው ለአምራች ኢንዱስትሪው የገበያ ትስስር ፈጥሮ ወደ አዲስ ገበያ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት አዳጋች ከከማድረጉም በላይ ሌሎች አምራች እንዱስትሪዎችም በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ምክንት የሚፈጠረውን መመሰቃቀል ለመቋቋምና በለውጡ ውስጥ እንዴት መዝለቅ እንደሚችሉ ገምግመው በስራው ለመዝለቅና ላለመዝለቅ እንዲውስኑ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የተጋረጠባትን ዘርፈ ብዙ ፈተና ማለትም ጦርነት፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የተንሰራፋ ስራ አጥነት፣ የተመናመነ ኢንቨስትመንት፣ አለም አቀፍ የንግድ መቀዛቀዝና በወጪ ንግዱ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በጥሞና ፈትሾና መርምሮ ምፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ምን ይደረግ

እና ምን ይደረግ የሚለው አስቸጋሪ ምርጫ ቢሆንም እርምጃ መውሰድ ግን ግድ ነው፡፡ ታዲያስ ምን ብናደርግ ይሻላል?

1. የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ሀሳብና አሁን እየተካሄደ ያለውን ጦርነትን ማቆም

መንግስት ለጊዜው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ ሀሳቡን ማቆም ይጠበቅበታል፡፡ ይልቅ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ የሀገሪቱን አንድነት በማጠናከር ላይ ቢያተኩር ይበጃል፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ጠርነት እየተካሄደና የሀገሪቱ ገቢ ለወታደራዊ ወጪዎች እየዋለ እድገትና ብልጽግና ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

2. ለጦርነት ይውል የነበረውን ወጪ በአለም አቀፍ ገበያ ሊሸጡ የሚችሉ ምርቶች እንዲመረቱበት ማድረግና ለሀገር ውስጥ ምርት የሚሆኑ ግብአቶችን ዋጋ መቆጣጠርና በአግባቡ መምራት፡፡

3. መንግስት ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የውጭ ገንዘብ ለሚልኩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትጵያውያን፣ ለቱሪስቶች፣ በአለም ገበያ ተፈላጊ ምርት ወደ ውጭ ለሚልኩ አካለት የተለየ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲያወጣ ( ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ማበረታቻ አስፈላጊ ነውና)፡፡

4. ከሀገሪቱ የገቢ አቅም ጋር አብረው የማይሄዱ የምርትና የአገልግሎቶች ፍላጎቶች እንዲቀንስ የሚያስችል የፋይናንስ ፖሊሲ ተግባረዊ ማድረግና በአለም ገበያ የሚፈለጉ ምርቶችን ለሚያመርቱ ማበረታቻ መስጠት፡፡

5. ለሀገሪቱ ምርትና አገልግሎቶች እድገት አስተዋጽኦ ለማያደርጉ እንደ የቅንጦት አፓርታማዎችና መዝናኛ ፓርኮች ያሉ ፕሮጀክቶችን ማቆም፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት አስተዋጽኦ ቢያደርም አዳዲሲ ምርትና አገልግሎቶችን ስለማይፈጥሩና እንደ ፍጆታ ስለሚቆጠሩ ሀገረቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ አስፈላጊ አይደሉም፡፡

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ በማድረጓ የውጭ ምንዛሪ እጥረቷን ልትፈታ እደማትችል እሙን ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የመፍትሄ ሀሳቦችና ሌሎች ስትራቴጂዎችንም ተግባረዊ ብናደርግ የውጭ ምንዛሪና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በቅጽበት እንደ ደመና ብን ብለው ይጠፋሉ ብሎ ማሰብም ከእውነታው ማፈንገጥ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ከማህበረሰቡ መስዋእትነት ከመንግስት ደግሞ ልዩ የአመራር ጥበብ ይጠበቃል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply