አንድ ለሰላም

ወቅታዊ የፖለቲካ ቅኝት


ኢትዮጵያ ምስቅልቅሏ የወጣው በአብይ አሕመድ የስልጣን ጥመኝነት ምክንያት ነው። ሰውዬው በአንድም በሌላም መንገድ ቢያንስ አስር አመት የስልጣን መንበሪቱን መቆጣጠር አለብኝ ብሎ የወሰነ ዕለት ነው፣ አገሪቱ ያለቀላት። የጋለ የብረት ምጣድ የሚያስንቅ መንበር መሆኑን አልተረዳም ነበረና ለስልጣኑ ሲል የማያደርገው ምንም ነገር አልነበረም። የትግል አጋሮቹን ከመካድና ማሳደድ ጀምሮ፣ በለማጅ የሴራ ፖለቲካ ተቀናቃኞቹን እስከመሰወርና መግደል ድረስ፣ ብሎም አለምን ጉድ ያሰኘ አረሜንያዊ ጦርነትና ጭፍጨፋ እስከማካሄድ ድረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። በሂደት ሁሉም ነገር ከቁጥጥሩ ውጭ ሲሄድ፣ ያቺን ተንኮል የሸረበባትን ቀን ሳይረግም አልቀረም። ወዳጅ መስለው ማኖ ያስነኩትን፤ ከጎኔ አሉ ሲላቸው ጊዜና ሁነት ጠብቀው በተራቸው የቆመሩበትን፣ ደግሞም ሊሰለቅጡት የዳዳቸውን የጥፋት አጋሮቹን፣ እየለቀመ ቆዳቸውን ገፍፎ ቢሰቅላቸው እንዴት በወደደ።

ዛሬ ከህወሓት ጋር ሰላም አውርጃለሁ ባለበት ቅጽበት፣ የአማራ ታጣቂዎች ላይ ለመዝመት የቆረጠበት ምክንያትም ይኸው ነው። በአማራ የተጀመረው ዘመቻ ከተሳካ፣ ተረኛው ሻዕቢያና የሻዕቢያ ጋሻጃግሬዎች ይሆናሉ። የሻዕቢያ ካድሬዎች በጊዜ አገሪቱን እየለቀቁ እየፈረጠጡ ቢመስልም፣ የገቡበት ድረስ ሊከተላቸው እንደሚችል ይገመታል። እነሱ ባሉበት ስጋትና ብጥብጥ እንጂ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል አብይ አሕመድ ተገንዝቧል። ከእርሱ እውቅናና ፈቃድ ውጪ ሻዕቢያ በጎን አማራን ሲያስታጥቅና ሲያሰለጥን ጊዜ ነው፣ አብይ አሕመድ ከሻዕቢያ ጋር የነበረው ግንኙነት ያበቃለት። ከሻዕቢያ ጋር ወዳጅነት ያተረፈለት ነገር ቢኖር ነውጥና ውድመት ብቻ ሲሆን፣ ከብዙ የውጪ መንግስታት ተነጥሎና በተለያዩ የማዕቀብ ማነቆዎች ተሸብቦ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅምና ሉኣላዊነት ማንኮታኮትና መፈናፈኛ ማጣትን ብቻ ነው ያተረፈው።

ያም ሆኖ አብይ አሕመድ ዕድለኛ ነው። የሚገባውን ያክል ትግልና ህዝባዊ አመጽ አልገጠመውም። የቱንም ያህል ቢጠላም፣ የተቀናጀ ትግል አልገጠመውም። ዛሬ አማራ ላይ ሲዘምት፣ አብዛኛው ህዝብ እጅና እግሩን አጣጥፎ፣ ድብድቡን እየተከታተለ ይገኛል። የአማራ ብሔርተኛ ሃይል (የአማራ ልጆች ሳይቀር ፋሽሽት ይሉታል) እድሉን ቢያገኝ ተራ ዜጎች ላይ ሳይቀር ምን ሊያደርግ እንደሚችልና እስከምን ርቀት ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ ባሉ ብሔሮችና ጎሳዎች ላይ የፈጸመውን አረሜንያዊ ድርጊት ሁሉም ታዝቧልና፣ አብይ አሕመድ በተራቸው ሲዘምትባቸው፣ አንድም ብሔር ወይም ጎሳ ከጎናቸው የመቆም ወኔም ፍላጎትም አይኖረውም።

ይህ ለአብይ አሕመድ ድርብ ድርብርብ ድል ያጎናጽፈዋል። ሰዉ ቁጥር አንድ ወንጀለኛውን አብይ አሕመድን መታገል ሲገባው፣ ሳይወድ በግዱ እየደገፈ፣ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ሃይል ላይ በጋራ መዝመት፣ የተለመደ የትግልና የኑሮ ስልት አድርጎታል። ምክንያቱም አብይ ቁጥር አንድ በህግ መጠየቅ ያለበት ወንጀለኛ ቢሆንም፣ የአማራ ፋሽሽቶችን ያህል ስጋት በሌላው ላይ አይጭርም። ልክ ትግራይና ኦሮሚያ ላይ ሲዘምት አማራው እንደደገፈው ማለት ነው። ያኔም ቢሆን አማራ አብይን የደገፈው፣ ከአብይ በላይ ኦሮሞና ተጋሩ ትልቅ ስጋት ናቸው ብሎ ስለሚያስብ ነበር። ያ ጨዋታ፣ ዛሬ በራሱ በአማራ ላይ እውን እየሆነ ነው።

የብዙዎች ጥያቄ፣ አብይ አሕመድ ከህወሓት ጋር መታረቅ ከቻለ፣ የአማራ ብሔርተኞች ከህወሓት ጋር መታረቅ ለምን አቃታቸው? የሚል ነው። ተወደደም ተጠላም፣ ሁለቱ ቡድኖችና እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ፣ በታሪክ አጋጣሚ እርስ በእርስ የተዛመዱ፣ ወደፊትም ተሳስረው የሚኖሩ ናቸው። ቢልላቸው በአንድ አገር ስር በሰላም የሚኖሩ፣ ካላለቸው ደግሞ በተለያየ አገር ውስጥ ሆነው በጉርብትና አብረው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። መጨረሻቸው ምንም ይሁን ምን እየተዳሙ መኖር አማራጭ ሊሆን አይችልም። የሚያዋጣው ሰላምን አውርዶ በሰላም መኖር ነው። የማይቀርለትንና ወሳኙን ሰላምን ዛሬ በግዜ ማስፈን ከቻሉ ደግሞ፣ ብዙ ነገሮች የሚስተካከሉበት ዕድል ሰፊ ነው።

ሰሞንኛው የኦሮሚያና የትግራይ ወዳጅነት፣ ከጀርባው በአማራ ስጋት የተቃኘ ነው። ስጋቱ ከሌለ አሰላለፍ እየቀየሩ ሌላ የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባት የሚያስፈልግበት አግባብ ሊኖር አይችልም። የአማራ ብሐርተኛ ቡድን ለድርድርና ውይይት ቅርብ ከሆኑት ከህወሓትና ከትግራይ ህዝብ ጋር ሰላም ቢያወርድ፣ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በተራቸው አማራን ከኦሮሞ የማግባባት ስራ እንደሚሰሩ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። የጦርነትን አስከፊነት አይተውታልና፣ የአሸማጋይ ሚና መጫወት ብርቃቸው ይሆናል። ኦሮሞም ቢሆን በስጋትና በግጭት ውስጥ መኖር የሚፈልግ አይመስለኝምና የሚያግባባው ከተገኘ ሰላም ማውረዱን የሚያስቀድም ይመስለኛል።

ዛሬ የአማራና የኦሮሞ ብሔሮች ከመቼውም ግዜ በከፋ ሁኔታ ውጥረት ላይ ለመሆናቸው አሌ አይባልም። ውጥረቱ እንዲበረታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ፣ ወንጀለኛው ሴረኛውና የስልጣን ጥመኛው አብይ አሕመድ ነው። በሁለቱ ህዝቦች መካከል እሳት እየጫረ፣ በኦሮሞ ዘንድ አጥቶት የነበረውን ድጋፍና ተሰሚነት መልሶ ለማግኘት እየተጠቀመበት ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ከህወሓት ጋር መታረቁ ያልተዋጠለት ሻዕቢያ አማራን ማጠናከር (ማሰልጠንና ማስታጠቅ) ስራዬ ብሎ በመያዙ፣ አማራ በአብይ አሕመድ ብቻ ሳይሆን፣ በኦሮሞ ብሔርተኞችም እንደ ትልቅ ስጋት ይታያል። የአማራ ብሔርተኞችም በተለይ ጽንፈኞቹ ዘውትር እንደሚያቅራሩትና እንደሚፎክሩት ከሆነ እንኳን ለሚመለከተው ጎሳና ብሔር ቀርቶ ለማይመለከተውም እንቅልፍ የሚነሱ ናቸው።

አማራ ከትግራይ ጋር እንዳይታረቅ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው፣ በጉልበት የያዘውን የምዕራብ ትግራይን መሬት አልለቅም የሚል አቋም ሊያራምድ መቻሉ ነው። ሰላም ከተፈለገ፣ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ የሚፈታው በህግና በውይይት ብቻ ነው። ወልቃይትን ከህግ ውጪ በጉልበት መያዝ፣ ነገ ፊንፊኔን በጉልበት ለመያዝ አመቺ ቅድመ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚሆን አማራ ልብ ሊለው ይገባል። ነገ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች የሚለው ተረት እንዳይተረትበት ዛሬ ነገሮችን በማጤን በብልሃት መንቀሳቀስ ይኖርበታል። የአገሪቱ የመጨረሻው ደመኛና የፍጻሜ ጦርነት የሚደረገው በአማራና በኦሮሞ መካከል ከሸገር የይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ እንደሚሆን መናገሩ ቀባሪን እንደማርዳት ይሆናል። የፍጻሜው ጦርነት በ”ፊንፊኔ ኬኛ”ና በ”በረራ የኛ” መካከል እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። አገሪቱ ወደዛ ታመራለች አታመራም የሚለውን ለመገመት ደግሞ፣ የወልቃይት ጉዳይ አያያዝንና የመጨረሻ ውሳኔን ማየት ብቻ በቂ ይሆናል። ስለሆነም አማራ አርቆ ማሰብ ተስኖት ለማያባራና የማታማታ ሽንፈትና ውርደትን ብቻ ለሚከናነብባቸው ዘርፈ ብዙ የጦርነት አውድማዎች ራሱን ከሚያጠምድ፣ ዛሬ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቹን በማስተዋልና በድፍረት ሊፈታ የሚችልበትን ዕድል ቢጠቀምበት፣ ለአማራም ለሌላው ዜጋም የሚጠቅም ይሆናል።

ኢትዮጵያን ለማትረፍና ትግሉን ወደ ተገቢው አቅጣጫ ለመቀየር፣ የአማራ ሚና ወሳኝ ነው። ከተራ መደናቆርና ብዥታ ወጥቶ የረዥም ዘመን ስኬት የሚጎናጽፍበትን፣ ጥቅሙንም የሚያስከብርበት፣ ቆራጥ ውሳኔ ዛሬውኑ መወሰን ይኖርበታል። አማራ ሰላም ያውርድ። ልዩነቱን በሰለጠነ መንገድ ይፍታ።

ሰላም!

@Gebeta Net

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply