ኮረና እና የኢኮኖሚ ጫናው

Post Reply
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

የዛሬ ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ የህክምና ባለሞያዎች አንድ አቤቱታ በጋራ እያሰሙ ነበር። በሶሻል ሚድያ ከፍተኛ ዘመቻ ተፈጥሮ ነበር። የደሞዝ ጭማሪ የሚጠይቅ ዘመቻ። የህክምና ባለሞያዎቹ የሚከፈላቸው የወር ደሞዝ፣ ዝቅተኛ በመሆኑና ከወር ወር መሰረታዊ ወጪያቸውን መሸፈን አቅቷቸው ሲቸገሩ ስለኖሩ፣ ብሎም ለሚሰሩት ስራ እውቅናና ምስጋና መነፈጋቸው ነበር ዘመቻውን የከፈቱት። ድሃ አገር ከየት አምጥታ አሁን ደሞዝ ትጨምርላችሁ ተብለው በተግሳጽ አርፈው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ ተመከሩና ጥያቄያቸውን አስይዘው ወደ ስራ ገበታቸው ተመለሱ። ዛሬ ባለስልጣኑም፣ ባለሀብቱም፣ ድሃውም ምኑም የሚተማመነው በነዚሁ ሰዎች ላይ ነው። አንድ በሉ።

ኮረና እንኳን የአገራችንን የማትረባ ኢኮኖሚ፣ የሃያላኑ አገራትን ኢኮኖሚም አንኮታኩቶ፣ ዲፕሬሽን ውስጥ ይከተናል ተብሎ እየተሰጋ ያለ አስጨናቂ ጉዳይ ነው። በኢኮኖሚክ ዲፕሬሽን ወቅት አትራፊ ብሎ ነገር የለም። ሁሉም ነው የሚከስረው። ኢኮኖሚው በጠቅላላ ነው የሚሽመደመደው። የሚተርፍ ሴክተር ወይም ዘርፍ አይኖርም። በሽታውን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚክና ማህበራዊ ኮንስክዬንሱን መወጣት የምንችለው ስንተባበር ብቻ ነው። እኔ ከማለት በፊት እኛን ማስቀደም ከቻልን ብቻ ነው። ሌላ መፍትሔ የለውም። ሁለት በሉ።

ከዚህ በሽታ ራስን ለመጠበቅ ሰዎች በቻሉት ፍጥነትና መጠን ሸማምተው ጎተራቸውን መሙላት ይመርጣሉ። ይሔ በተናጠል ስናዬው በጣም ራሽናል ውሳኔ ነው። እንደማህበረሰብም ብናዬው የምርት እጥረት (ችግር) ባይኖር ኖሮ መልካም ነገር ነበር። የበሽታውን ስርጭት የሚቀንስና ለሁሉም የሚበጅ እርምጃ ስለሆነ። ነገር ግን የአቅርቦት ችግር አለ። አብዛኛው ሸቀጥ የሚመጣው ከውጭ ነው። በውጭው አለም ደግሞ እንቅስቃሴዎች እየተገደቡ ነው። ፋብሪካዎች ለግዜው እየተዘጉ፣ ሰራተኞች ቤታቸው እንዲቀመጡ እየተደረገ ነው። ስለሆነም ኢምፖርት ማድረግ ብንፈልግና አቅሙ ቢኖረን እንኳን በአለም ገበያ የምርት እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። ፈተናው ቀላል አይደለም። ይህን በገበያ ስርዓትና በሰላም ግዜ በምንከተለው ስልት ሳይሆን፣ በክራይስስ ግዜ አገርና ህዝብን ከጭንቅ ለማውጣት በሚያስችል ስልት በጋራ ልንወጣው የሚገባ የጋራ ችግር ነው። ሶስት በሉ።

ለተፈጠረው ችግር የሚመጥን ሪአክሽን ማህበረሰቡ ሲያደርግ፣ በብዙ ሸቀጦች ላይ ያልተጠበቀና ከወትሮው የተለየ የተጋነነ ፍላጎት ይፈጠራል። እየተፈጠረም ነው። ይህንን ኢንፊሌትድ ፍላጎት ግምትና በስቶራቸው ውስጥ ያለውን አነስተኛ ክምችት ግምት ውስጥ አስገብተው፣ የኮረና ፍራቻ የፈጠረውን የተለጠጠ የሰዉን የመክፈል ፍላጎት (Willingness To Pay) ግምት ውስጥ አስገብተው፣ በጭንቅ ግዜ ሊጠየቅ የማይገባ ዋጋ እየጠየቁና እየተመኑ፣ የአጭር ግዜ ትርፍ ለማካበት ሲሞክሩ፣ አንዳንድ ስግብግብና "መሃይም" ነጋዴዎች ገበያውን ወደ ለየለት ቀውስ እየከቱት ይገኛሉ። ባለው እጥረት ላይ አርቴፊሻል እጥረት ጨምረህ ዋጋ እንዲንር ካደረግክ ብኋላ ሆርድ ያደረግከውን ምርት ባልተገባ ዋጋ ሸጠህ ለማትረፍ መሞከር እውቀት ወይም ችሎታ አይደለም። ህሊና ቢስነትና አላዋቂነት ነው። በዚህ ቀውስ ውስጥ በዚህ መንገድ ጥቂት ነጋዴዎች የተወሰነ ብር ሊያተርፉ ይችላሉ። ነገር ግን ለበሽታው ስርጭትና ለብዙዎች እልቂት ካታሊስቶች መሆናቸውን ሊዘነጉት አይገባም። እነሱ ከሚያገኙት ብዙ እጥፍ በላይ ገበያው ተናግቶ፣ አገሪቱ ልትወጣው የማትችል ቀውስ ውስጥ በመክተት፣ የራሳቸውን ህይወትም በተዘዋዋሪ አደጋ ላይ መጣላቸው አይቀሬ ነው። ኮረናን በጋራ ካልተከላከልከው አገሪቱ የለየለት ቀውስ ውስጥ ከገባችና በሽታው ሁሉንም ባንዴ ያዳረሰ እለት፣ የፈለገውን ያህልና ብርና ስልጣን ቢኖርህም አትተርፍም። ብትተርፍም ነገ የኔ የምትለው ነገር አይኖርህም። አራት በሉ።

በርበሬ ነጋዴ የበርበሬ ዋጋ ላይ ድራማ ሲሰራ፣ የጤፍ ነጋዴ የጤፍ ዋጋ ላይ ድራማ ሲሰራ፣ ወዘተ ሁሉም በየተሰማራበት ድራማ መስራቱን አያቆምም። ምክንያቱም የተወደደውን ኑሮ ለመሸፈን ለሚሰጠውን አገልግሎትና አቅርቦት ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል። ይህ የዋጋ ግሽበትን ብቻ ነው የሚፈጥረው። ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። በርበሬ ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረገው፣ ዘይት ላይ የተደረገ ጭማሪ ላይ ያጣጣዋል። ትርፍ የለም። ግሽበቱ ሲንር ከምንም በላይ የሚጎዳው በአነስተኛ ደሞዝ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጠው የመንግስት ተቀጣሪ ነው። መንግስት አምና ደሞዝ ጭማሪ ማድረግ ያልቻለውን ዘንድሮ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ላይ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ በፍጹም አይታሰብም። እናም ህይወታችንን ይታደጉልናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸው የህክምና ባለሞያዎች ጭምር በዚህ ስግብግብ የነጋዴዎች ባህሪ ይጠቁና ተማሚዎችን ለማከም ራሳቸውን ለበሽታው የሚያጋልጡት አንሶ፣ የምግብ ወጪያቸውን እንኳን መሸፈን እንዳይችሉ አድርገን ካዳከምናቸው፣ እንዴትና በምን ሁኔታ የሙያ ግዴታቸውን ሊወጡ ይችላሉ? እንደትላንቱ በጋራ አድማ ባይመቱም፣ አንድ በአንድ ከስራው ሊሸሹ ይችላሉ። ባይሸሹም ህይወታቸውን ሰጥተው የቻሉትን ያህል አገልግለው መስዋእት ይሆናሉ። የዛሬ የነጋዴው መስገብገብ መጨረሻ ሔዶ ሔዶ የሚደርሰው እንዲህ አይነት አስከፊ ሴናሪዮ ላይ ነው። ያኔ ብር አያድናቸው። ሆርድ ያደረጉት ጥራጥሬ አያድናቸው ማህበረሰቡን ለበሳ ምስቅልቅ ዳርገው ከነሀብታቸው ወደማይቀረው ይሔዳሉ። ለምሳሌ ነው የህክምና ባለሞያዎችን ያነሳሁት እንጂ፣ በየዘርፉ የተሰማሩ በዝቅተኛ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ የህብረተሰቡ ክፍል በዚህ የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ባህሪ ሲመቱ፣ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ተመሳሳይ ነገር ነው። እናም እዛ ቦታ ውስጥ ራሳችንን ሳናገኘው በፊት ከእንዲህ አይነት ድርጊት ተቆጥበትን ይቺን የፈተና ግዜ እየተባበርን በአንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መንፈስ ወደፊት መራመድ ይበጀናል። መንግስት እያሳደደ ሱቅ ስላሸገ መፍትሔ አይሆንም። ይህ ባህሪያቸው ሊያስከትል የሚችለውን የትየሌለ ኮንስኰንስ ልብ እንዲሉት በየሚድያውና በየተገኘው አጋጣሚ ማሳወቅ የተሻለ ይመስለኛል። አምስት አላችሁ። አይ ሬስት ማይ ኬዝ።
Post Reply