ኮቪድ19 ጠቃሚ መረጃዎች

User avatar

yaman
Posts: 86
Joined: Mon Sep 11, 2017 12:50 pm

@Endalamaw Abera

የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ትክክለኝነት መለኪያዎች
======================================

የሕክምና አገልግሎትን ቀረብ ብሎ ያየ ሰው ሁሉ እንደሚያውቀው አንድ በሽታ መኖሩን ወይም አለመኖሩን ለመፈተሽ የሚያገለግሉ የተለያዩ የላቦራቶሪ ምርመራ ዘዴዎች ይኖራሉ፡፡ ብዙ ሰው በጥልቀት ላይገነዘበው ይችላል ብዬ የምገምተው አንድ የላቦራቶሪ ዘዴ ለመደበኛ አገልግሎት የሚመረጥባቸው መስፈርት ምንድን ናቸው የሚለው ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ይህን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

ለመነሻ ያህል
----------------
በላቦራቶሪ ምርመራ ማግኘት የምንፈልገው ውጤት በሽታው ካለ ፖዚቲቭ፣ ከሌለ ኔጌቲቭ መሆኑን እንዲነግረን ነው፡፡ በገሃዱ ዓለም ግን የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት 4 አይነት ሊሆን ይችላል፤ እነዚህን ውጤቶች ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ እንበላቸው፡፡ ይኸውም

ሀ = በሽታው ኖሮ ውጤቱ ፖዚቲቭ ሲሆን
ለ = በሽታው ሳይኖር ውጤቱ ፖዚቲቭ ሲሆን
ሐ = በሽታው ሳይኖር፡ ውጤቱ ኔጌቲቭ ሲሆን
መ = በሽታው ኖሮ ውጤቱ ኔጌቲቭ ሲሆን

በዚህ መሠረት ሀ እና ሐ ትክክለኛ ውጤቶች ሲሆኑ፣ ለ እና መ ደግሞ የተሳሳቱ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የውጤት አይነቶች በላቦራቶሪ ቋንቋ “Gold standard” የሚባል መመርመሪያ ከሚሰጣቸው ውጤቶች ጋር በማነፃፀር የሚገኙ ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ የምርመራ አይነት Gold standard አለ፡፡ (ለተጨማሪ መረጃ ጉግልን ይጠቀሙ፡፡)

በዕለታዊ ሥራችን የምንጠቀምባቸውን የላቦራቶሪ ምርመራ ዘዴዎች ከምንመርጥባቸው መስፈርት አንዱ እነዚህን መሠረት ባደረገ ስሌት የሚደረስበት ነው፡፡ ስሌቱን ለመነካካት ያህል

* ድምሩ እውነተኛ ፖዚቲቭ በምርመራ ትክክል ፖዚቲቭ የተባለውንና በስህተት ኔገቲቭ የተባለውን ያጠቃልላል፡፡
* ድምሩ እውነተኛ ኔጌቲቭ በምርመራ ትክክል ኔጋቲቭ የተባለውንና በስህተት ፖዚቲቭ የተባለውን ያጠቃልላል፡፡

ከዚህ ተነስተን በእንግሊዝኛ ሴንሲቲቪቲ (Sensitivity) እና እስፔሲፊሲቲ (Specificity) የሚባሉ መለኪያዎችን እናሰላለን፡፡ ሂሳቡን ማየት ለምትፈልጉ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሴንሲቲቪቲ =ሀ/(ሀ +መ)
እስፔሲፊሲቲ=ሐ/(ሐ+ለ)
pos-neg.jpg
pos-neg.jpg (26.14 KiB) Viewed 7699 times
.
አንድ የምርመራ አይነት ከፍተኛ ሴንሲቲቪቲ አለው ሲባል ፖዚቲቭ የሆነን ናሙና በስህተት ኔጌቲቭ የማለት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት ነው፡፡ ከፍተኛ እስፔሲፊሲቲ ካለው ደግሞ ኔጌቲቭ የሆነን ናሙና በስህተት ፖዚቲቭ የማለት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት ይሆናል፡፡

በሕክምና ሥራችን አንድን ሰው መርምሮ ውጤት ለመስጠት የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች በጣም ከፍተኛ ሴንሲቲቪቲና እስፔሲፊሲቲ እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ለምሳሌ ለኤችአይቪ ምርመራ የምንጠቀምባቸው ስልቶች በሁለቱም መስፈርት ከ99% በላይ ናቸው፡፡ ለበሽታ ቅኝት ሲሆን ግን ከዚህ ያነሰ አስተማማኝነት ያለቸውንም መመርመሪያዎች ልንጠቀም እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ የምንፈልገው የስርጭቱን አዝማሚያ ለመከታተል (ከዓመት ወደ ዓመት ቀነሰ፣ ጨመረ፣ ወይስ ባለበት ቀጠለ ለማለት) እንጅ ተመርምረው ፖዘቲቭ የሆኑትን ለማከም፣ ኔጌቲቭ የሆኑትን ወደቤታቸው እንዲሄዱ ለማሰናበት ስላልሆነ ነው፡፡

ለማጠቃለል
----------------
ለሥራችን የምንጠቀምባቸውን የላቦራቶሪ ምርመራ ዘዴዎች ለመምረጥ የምንጠቀምባቸው መስፈርት በርካታ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል ዋነኞቹ

* የምርመራው ዓላማ (ሕክምና፣ ምርምር፣ የበሽታ ቅኝት)
* አስተማማኝነት
* ዋጋ (ለበሽተኛው፣ ለአገልግሎት አቅራቢው)
* ለማከናወን የሚፈልገው መሣሪያና የሰው ኃይል (የረቀቁ ማሽኖች፣ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ምርመራዎች በስፋት ለመጠቀም አመቺ አይደሉም)
* ውጤቱን ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ
* ሌሎች (ለምሳሌ.. ጥሩ መመርመሪያ የሚያመርት ድርጅት በማዕቀብ ምክንያት ለፈላጊው አገር ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡)

መልካም ቀን

"I have great faith in fools; self-confidence my friends call it." - Edgar Allan Poe

Post Reply