ስለ ኮረና ዝም አንበል

User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

በዚህ ዓምድ አይነኬ የሚመስሉ አንኳር ጉዳዮች ጭምር ስለ ኮረና እንደወረደ ሀሳቤን አካፍላችኋለሁ።

ኢትዮጵያ ለከፋ አደጋ የተጋለጠች ከሚያደርጓት ፋክተሮች አንዱ ባህላችን ነው። የታመመ ሰው በአካል ሔዶ መጠየቅ፣ የሞተ ሰው ተሰብስቦ መቅበር፣ ለቅሶ መድረስ፣ ወዘተ በደህናው ግዜ የምንኮራባቸው ጥልቅ እሴቶቻችን ናቸው። ለዚህ በሽታ ግን ቁልፍ የስርጭት መንገዶች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። በሽታውን መቆጣጠር ተችሎ እዚህ ችግር ውስጥ ባንገባ ይመረጣል። ችግሩ ገፍቶ ከመጣ ግን ለመምረጥ የምንገደድበት ሁኔታ ይኖራል።

ሰው ሲታመም ሔዶ መጸለይ፣ ሲሞት መገነዝ፣ ፍትሃት ማድረስ፣ ምን ማለት ባህላችን ነው። በዚህ ስራ የተሰማሩ የእምነት አባቶች እንደ ሀኪሞች ሁሉ ራሳቸውን ለበሽታው ያጋለጡ ናቸው። ልዩነቱ ሀኪሞች ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የእምነት አባቶቹ ጥንቃቄ የማድረግ ልማዳቸው ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም በሽታውን በማሰራጨት የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። እናም ለእምነት አባቶችም ጭምር እንደሌላው ሁሉ እጅ ከመንሳት ውጭ መዳፍና መስቀል መሳለም ራስን ለአደጋ ያጋልጣል።

(ለእምነት አባቶች ለየት ያለት የማንቂያ ትምህርት በተለያየ መንገድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል። )

በኮረና ምክንያት እስካሁን የሞተ መኖሩ ባይታወቅም፣ ይህን ማውሳቱ ለቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ይረዳል ብዬ አምናለሁ።
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

ጣልያንን አይተን ካልተማርን፣ ካልተዘጋጀን፣ ትልቅ ፈተና ላይ ነን። በኢኮኖሚ አቋም ከኛ አገር በብዙ እጅ የምትሻል አገር፣ የተሻለ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት አገር፣ በቁጥርም በጥራትም ከኛ አገር የተሻለ የህክምና ባለሞያ ያላት አገር፣ በዚህ በሽታ በየቀኑ እያጣችው ያለ ህዝብ ቁጥር ለማሰብ የሚዘገንን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ኮረና ታየ ከተባለ ቢያንስ አስር ቀን ይሆነዋል። እስካሁን ፖዚቲቭ ናቸው የተባሉ ሰዎች ቁጥር 9 ብቻ ነው። እኔ በምኖርበት አገር በአስረኛ ቀኑ ወደ 500 ተጠግቷል። ያውም የታወቀው ብቻ ነው። እዚህ እንደ እኛ አገር በተገናኘህ ቁጥር መጨባበጥና መተቃቀፍ የለም። የትራንስፖርት አገልግሎት እንደኛ የተጨናነቀ አይደለም። ኑሯቸው በአንጻራዊነት ሶሻል ዲስታንሱን የጠበቀ ነው። ያም ሆኖ ወረርሽኙ በአንድ ግዜ ተዛምቶ 500 በላይ ደረሰ።

ኢትዮጵያን ስንመለከት ደግሞ፣ አዲስ አበባ ብቻ ያለው የህዝብ ብዛት፣ ከኖርወይ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ይበልጣል። ኑሯችን የተጨናነቀ ነው። ገበያው፣ ቸርቹ፣ መስጊዱ፣ ባሱ፣ ታክሲው፣ ምኑ በህዝብ ጢም ያለ ነው። በዚህ ሁኔታ ከ10 ቀን በፊት የታየው በሽታ አሁን ድረስ 9 ብቻ ናቸው አክቲቭ ኬዝ ላይ ያሉት ብሎ መዘናጋት የዋህነት ነው። ምልክቱ ሳይታይባቸው ወይም መጠነኛ ምልክት ብቻ እየታየባቸው የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሊኖሩ እንደሚችሉና ከቀን ወደ ቀን ይህ ቁጥር እየጨመረ ሊሔድ እንደሚችል ገምቶ ጥንቃቄና አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከብዙ አገራት ልምድ በመነሳት የቫይረስን ስርጭትን ስናጤነው፣ ስርጭቱ የሚያድገው ኤክስፖኔንሺያሊ ነው። ኢትዮጵያ ሲደርስ የተለየ የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም።

አዝናለሁ በጣም፣ ነገር ግን መሪዎቹ የረቡ አይደሉም። ከጥቂት ሳምንታት ብኋላ አገሪቱ ልታስተናግድ የምትችለውን ጭንቅ የተረዱ አይመስሉም። በየአጋጣሚው መሰብሰብንና ስብሰባን የሚያበረታታ ስራ ሲሰሩ ነው እያየን ያለነው። ምርጫውን ምኑን እርሱት። ከጥቂት ጊዜያት ብኋላ፣ አገሪቱ በአንድ እግሯ ልትቆም ትችላለች። በተለያዩ አገራት እያየን ያለነው እውነታ ይኸው ነውና። እናም የረባ መሪ ስለሌላችሁ ራሳችሁን ጠብቁ።

ራሳችሁን በስብስብ ውስጥ አትክተቱ፣ ከሰው ጋር መገናኘትን ቀንሱ። ከችላችሁ በእግራችሁ ወይም በሳይክል ወይም በግል መኪና ተጓዙ፣ ፐብሊክ ትራንስፖርት መገልገል ቀንሱ። መጨባበጥ፣ ጉንጭ ለጉንጭ መሳሳምና መተቃቀፍ አስወግዱ። እጃችሁን በደንብ ታጠቡ፣ ሳትጣቡ ምግብ እንዳትበሉ። ፊታችሁን አትነካኩ። ከቻላችሁ ቤት ሆናችሁ ስሩ። ጉንፋን ከያዛችሁ አስፈቅዳችሁ ቤት ተቀመጡ፣ ከቤት ሆናችሁ ስሩ። ራሳችሁን ጠብቁ።

በነገራችን ላይ ለኛ ለአረጋውያን ስትሉ የሚለው ማስታወቂያ ትክክል አይደለም። ቫይረሱ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎችን በተለየ የሚያጠቃ ቢሆንም፣ ብዙ ሰው በአንድ ግዜ ከታመመና የህክምና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ ከሔደ፣ ማን ሊተርፍ ማን ሊያመልጥ እንደሚችል አይታወቅም። ጣልያንን የገጠማት ያ ነው። እናም ጥንቃቄው ለእያንዳንዳችን ስንል የምናደርገው ነው።
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

የኮረና ቫይረስ በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የከፋ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ምክንያት
  • በቲቢ የሚሰቃይ፣ ኤችአይቪ ያለበት፣ በ(ቢጫ) ወባ የሚሰቃይ፣ ስኳር ኩላሊትና ጉበት በሽታ ያለበት፣ ካንሰር ያለበት፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለከባድ የጤና እክል የሚጋለጥ፣ ጧሪ የሌላቸው የእድሜ ባለጸጋዎች፣ ወዘተ በብዛት ያሉበት አገር ስለሆነ። እነዚህ በቫይረሱ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ናቸው።
  • የኑሮ ዘይቤው ወረርሽኙን ለመግታት ከባድ ያደርገዋል።
  • ድህነት አለ። የውሃ እጥረትና የመጸዳጃ ቁሳቆሶች እጥረት አለ።
  • ዘርፈ ብዙ የአመለካከት ችግርም አለ።
  • የተጨናነቀ የከተማና አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ ስርጭቱን የሚያፋጥኑ ፋክተሮች ናቸው።
  • ከውጭ አሁንም በሽታው ያለባቸው ሰዎች መግባት ይችላሉ።
  • በሽታው በታየባቸው ከተሞች የመንቀሳቀስ ገደብ አልተቀመጠም። እንደልብ መውጣትና መግባት ይቻላል።
  • ወዘተ
ለፖለቲካ ፍጆታና ለምርጫ ማዳመቂያ ከሚደረገው እርምጃ ( የፎቶ ዘመቻ) ባሻገር ዲሳይሲቭ የሆነ እርምጃ ካልተወሰደ፣ የብዙዎች እጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። በዚህ ዝግጅታቸው የጤና ባለሞያዎችም አደጋ ላይ ናቸው።

የጨለማ ነብይ አይደለሁም፣ ነገር ግን እየሆነ ካለው ተነስቶ የሚሆነው መገመት አይከብድም።
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

13. mar 12:50 · ኮረና አዲስ አበባ ገብቷል። መርካቶ ከገባ አለቀ። የመዛመት እድሉ በአስር እጥፍ ይጨምራል። ታድያ ከምንም በላይ የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋል። ይህን በሽታ እንደ ኤችአይቪ አላስፈላጊ ታቡ እንዳንለጥፍበት። ጉንፋን ነው። ከተለመደው ጉንፋን ለየት የሚያደርገው፣ አዲስ መሆኑ፣ ፈጥኖ የሚዛመት መሆኑና የተዳከመ ኢምዩን ሲስተም ያላቸውን ሰዎች ለሞት የሚዳርግ መሆኑ ነው። የጉንፋን ሲይምፕተም ያለው ሰው ከሌሎች መራቅ አለበት። ሌሎችም ጉንፋን ከያዘው ሰው ንኪኪ እንዳይኖራቸው መጠንቀቅ አለባቸው። ከዛ ባሻገር እከሌ የኮረና ቫይረስ ተሸካሚ ነው፣ እከሌ ነው የበከለን፣ እከሌን እንዳትጠጉ፣ ምናምን አይነት አላስፈላጊ ዘመቻ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በተጨማሪም እኔ ኮረና በተለየ ሊያጠቃቸው ከሚችል የማህበረሰብ ክፍል አይደለሁም ብሎ መዘናጋት አያስፈልግም። በመተሳሰብና በቅንነት ካልሆነ፣ ጣት በመቀሳሰርና በማንአለብኝነት፣ ጉዳዩን ከያዝነው የሚተርፍ ሰው አይኖርም። ንጽህናችንን እንጠብቅ። ከወዲሁ መዘጋጀትና መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው።
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

ኮረና በርካታ አገራትን ያልተጠበቀ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እየከተተ ነው። የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ወይም ለመቀነስ የሚረባረቡ አገራት፣ ኢኮኖሚያቸውን በቀጥታ ሊጎዳ የሚችል መጠነ ሰፊ የፖሊሲ እርምጃ ወስደዋል። የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋል። ሁሉም ሰው ቤቱ እንዲቀመጥ ትዕዛዝ ተላልፏል። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ከስራ ተሰናብተዋል። የግል ድርጅቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ተከናንበዋል። ይህ ሁሉ በሽታው በአንድ ግዜ ሁሉም ዘንድ እንዳይደርስና በቀስታ የሚያዳርሰውን አዳርሶ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲባል ነው። ይህ በእነ ኖርወይ የመሳሰሉ አገራት የምናየው እርምጃ ነው። ኢኮኖሚው ክፉኛ ተነክቷል። በሽታው ግን እስካሁን ለከፋ አደጋ አገሪቱን አላጋለጣትም። ብዙ ሰው ቢታመምም፣ የሞተው ቁጥር አነስተኛ ነው። የህክምና ተቋማት፣ ከሚችሉት በላይ በሽተኛ አልፈለሰባቸውም።

በሌላ በኩል የመጣው ይምጣ እንቋቋመዋለን በሚል እምነት ኢኮኖሚውን የሚጎዳ መጠነ ሰፊ እርምጃ ሳይወሰድ፣ ሰዉ ከዕለታዊ ኑሮው ሳይስተጓጎል፣ የቻሉትን ያህል በምክርና በህክምና እርዳታ በሽታውን ማስታመም ነው። ይህ በእነ ጣልያን የመሳሰሉ አገራት የምናየው ነው። ዛሬ በሽታው በጣልያን ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ፣ የሺዎችን ህይወት ቀጥፎ፣ የሚልዮኖችን ኑሮ አናግቶ፣ ኢኮኖሚውን ዛሬ ማሽመድመድ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የማገገም አቅሙን ያዳከመና የህዝቡን ስነልቦና የሰለበ ክስተት ሆኗል።

ከስር የተቀመጠው ግራፍ የሚያሳየው በአጭሩ እነዚህን ሁለት ሁኔታዎችን ነው። ኮረና ቫይረስ መድሃኒት የለውም። በመሆኑም ጣልቃ ገብተን ከርቩን ፍላት እናድርገው ወይስ የመጣው ይምጣ ብለን እንጋፈጠው ነው ጥያቄው። በአንዴ ተከምሮ ሲመጣ መቋቋም የሚችል አቅም ካለን ብቻ አሁን ባለው ሁኔታ እንቀጥላለን። አለበለዚያ ግን የሚጠብቀንን መገመት አይከብድም።
covid.png
covid.png (12.7 KiB) Viewed 19789 times
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

የCOVID-19 ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ ዛሬ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንደኛው "ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ሁሉ በራሳቸው ወጪ ለዚሁ ዓላማ በተወሰኑ ሆቴሎች ውስጥ ለ14 ቀናት ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ" ኮሚቴው ወስኗል ይላል። ብዙዎቹ ወጪያቸውን ለመሸፈን ይቸገራሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን ለአጭር ግዜ፣ በሆነ ጉዳይ፣ ወጣ ብለው የገቡ ሰዎች ይህ ወጪ ሊከብዳቸው ይችላል። ከወጪው ለማምለጥ ሲሉ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡን ለበሽታው ሊያጋልጡ ይችላሉ። በመሆኑም ወጪህን መሸፈን ግዴታ ሳይሆን በውዴታ ቢሆንና ለማይችሉ መንግስት ወጪውን ቢሸፍንላቸው ይመከራል። አገር ለሚያምሱ ፖለቲከኞች ሳይቀር የኢትዮጵያ ህዝብ ለሁለት ዓመታት ሆቴል አስቀምጦ ሲቀልብ ኖሯል። ለ2 ሳምንት ምን አላት!
User avatar

Topic author
gebetaforum
Site Admin
Posts: 71
Joined: Fri Aug 18, 2017 12:12 am
Contact:

ምን ላይ ሞክሮት እንዳገኘው ባላውቅም፣ መድሀኒቱን አግኝቼዋለሁ፣ የምሞክርበት በሽተኛ ነው ያጣሁት፣ የሚል ዜና ባለፈው ሳምንት ስሰማ ብዙም ትኩረት አልሰጣሁትም ነበር።። አሁን ግን ቁጥራቸው ተበራከተ። እጄ ላይ አስቀምጦት አሸዋ ሲሆን አየሁ ከሚለው ነብይ ነኝ ባይ አጭበርባሪ ጀምሮ፣ እነ WHO የሚሰጡትን ምክር (በሳሙናና በሳኒታይዘር መታጠብና ንጽህናን መጠበቅ) እስከሚያጣጥለው የባህል ሀኪም ነኝ ባይ፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው ለመቀፈል ሲዳክሩ ሳይ የህዝቡ ፈተና ከጠበቅነው በላይ ከባድና ውስብስብ እንደሚሆን ታየኝ። ህግና ስርዓት አስከባሪ ካለ፣ እንዲህ ዓይነት ወፈፌዎችን አደብ ማስገዛት አለበት። አለበለዚያ ህዝቡን ለእልቂት ይዳርጉታል። ዜጎችን በማዘናጋት ለበሽታው በማጋለጥ፣ የኮተታቸው መሞከሪያ አይጥ፣ የድራማቸው ሲሳይ ማድረጋቸው አይቀርም። በጥብቅ ሊወገዙና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።
Post Reply