የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት እና አዲሱ የፖለቲካ አሰላለፍ
ወቅታዊ የፖለቲካ ቅኝት
የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ። ጉብኝቱ ትልቅ ጂኦፖለቲካዊ እንደምታ እንዳለው ተገልጿል።
ላለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ሶስትዮሽ የሰከረ ግኑኝነት በጥቂቱ ሲቃኝ የነበረ የቀጠናው ጂኦፖለቲካ፣ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ብኋላ ኢትዮጵያና ኬንያ መሪ ተዋንያን ሆነው እንዲወጡ እየተሰራበት ይመስላል።
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያና ለኬንያ የ25 ሚልዮን ዩሮ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ካጠቃላይ የተመደበው እርዳታ 22 ሚልዮኑ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ይህ እንድቅስቃሴ ስጋት ውስጥ የከተተው የኤርትራው አምባገነን ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከትላንትና ወዲያ ለአገሪቱ የስቴት ሚድያ በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ ራሱን የቀጠናው ብቸኛ ተዋናይ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ እየራቀና ዳግም እየተነጠለ ያለበትን ሁኔታ የሚያመላክት ቃለ መጠይቅ ነበር ያደረገው። ኤርትራ ዳግም ወደ ቅዝቃዜው ተጥላ በሩ እየተቆለፈባት ይመስላል። (በሪአማን ነው በትሪአማን የሚባለው?)
አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላም ድባብ አድንቃለች፣ ድጋፏን እንደምትገልጽና ለጋራ ጥቅም እንደወትሮው ሁሉ በጋራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ዳግም አረጋግጣለች። የሰላም ጅምሩ የተሟላና ለዘለቄታው የተሳካ እንዲሆን የኤርትራ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ከትግራይ መሬት ለቆ እንዲወጣ እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ አመራሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት አግባብ የፍትሕ ሒደት መጀመር እንደሚገባ ገልጿል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ብኋላ፣ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የዛንዚባሩ ውይይት፣ ያለ ስምምነት ተቋጭቷል። ይህ የመጀመሪያ ዙር ነው የተባለለት በኢትዮጵያ መንግስትና በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ሰራዊት መካከል የተካሔደው ውይይት፣ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የታዩበት ውይይት ነበር ተብሏል። በሁለቱም ወገን የነበሩት ተወያዮች፣ በአለመግባባታቸው ተግባብተው፣ ለሌላ ዙር የውይይት መድረክ ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከፕሪቶሪያ ድርድር ብኋላ፣ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት፣ የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ በአማራ ክልል የጀመረው አዲስ የህግ ማስከበር ዘመቻ ከዚህ መርሁ ጋር የሚጣረስ አደገኛ አካሔድ መሆኑን ብዙዎች ይጠቅሳሉ። ሌላ አላስፈላጊ ደም መፋሰስ እና ውድመት ከመድረሱ በፊት፣ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፈታት የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ለሁሉም ጠቃሚ ይሆናል።
በእርግጥ ለፕሪቶሪያም ሆነ ለዛንዚባር የድርድር መድረኮች መንግስት ለመቀመጥ የተገደደው፣ በእነ አሜሪካ መንግስት እና በነ አይኤምኤፍ የመሳሰሉት ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በደረሰበት ጫና መሆኑን አሌ አይባልም። አገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለመታደግ ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ብድር እና የብድር አከፋፈል አግባብ ማሻሻያ እንዲደረግለት መንግስት በጠየቀ ግዜ፣ እነአይኤምኤፍ እና የአሜሪካ መንግስት፣ ያስቀመጡለትን ቅድመሁኔታ (የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ፣ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ወዘተ) ካልተገበረ በስተቀር የሚያስፈልገውን ብድር ሊሰጡት እንደማይችሉ ግልጽ ባደረጉበት ወቅት ነበረ ለድርድር ለመቀመጥ የተገደደው።
ሆኖም በአማራ ክልል የገጠመውን ችግር በተመሳሳይ የውይይት መድረክ ለመፍታት፣ የውጭ ጫናና ግፊት የግድ መፈጠር የለበትም። በሰላም ሂደቱ እያገኘ ያለውን ጥቅምና ሌጅቲሜሲ በመረዳት፣ የሰላም ሂደቱና ተያይዘው እየተገኙ ያሉ ጥቅሞች እንዳይቀለበሱ መንግስት አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል።
ከህወሓት እና ከኦነግ ጋር ሰላም ማውረድ እያስገኘለት ያለውን ጥቅም በመገንዘብ፣ መንግስት በአማራ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች እየገጠሙት እና ሊገጥሙት የሚችሉትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታት ልማዳዊ አሰራር ሊያደርገው ይገባል።
በማጠቃለል ፋኖ የሚባለው አደረጃጀት ከመሪ አልባ አደረጃጀት ያልተናነሰ አስቸጋሪ አደረጃጀት በመሆኑ፣ “መደበኛ” ግጭቶች ወደ ለየላቸው የሲቪልያን የእርስ በእርስ ጦርነት ሳይቀየሩ በፊት መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት የሰከነ አካሔድ ችግሩን ሊፈታው ይገባል እንላለን።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!