ከምጽአተ-ኢትዮጵያ እንተርፍ ይሆን?

ባይዋጥልዎም እነሆ ፖለቲካ…!

በልደቱ አያሌው

ምጥን ሐሳብ

ብዙ ውድመትና እልቂት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ ዛሬ ላይ አብዛኛው ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሙሴነት” ተስፋ ቆርጦ ተቃዋሚ ሆኗል። ከመቃወምም አልፎ አገዛዙን ለማስወገድ እየታገለና መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል። በዚህም ምክንያት “አገዛዙ አልቆለታል፣ የምንፈልገው ለውጥም እውን ሊሆን ተቃርቧል ” የሚል አመለካከት በተቃዋሚው ጎራና በሕዝቡ ውስጥ በሰፊው ተፈጥሯል።
ይሁንና የወቅቱ የትግል ሂደት በበርካታ ነባርና አዳዲስ ድክመቶች የተሞላ ነው። ተቃዋሚው ጎራ አገዛዙን ከመተቸትና አምርሮ ከመቃወም ባለፈ እስካሁን በራሱ ዙሪያ ያሉትን ድክመቶች በሀቅ የመገምገም ና የማረም ድፍረትና ፍላጎት ኖሮት አያውቅም። ነገር ግን እነዚህ ድክመቶች በበቂ መጠን ካልተወገዱ በስተቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩና አገዛዛቸው ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድል ሊያገኙ፤ በሆነ አጋጣሚ ከስልጣን ቢወገዱም እንኳን “ድህረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ ” ህልውናዋን አስጠብቃ የመቀጠል ዕድሏ እጅግ ጠባብ ይሆናል።እንደ እስከአሁኑ ሁሉ ወደፊትም የአገዛዙ በስልጣን ላይ “የመቀጠል ወይም ያለመቀጠል ” ዕድል በዋናነት የሚወሰነው በራሱ ድክመትና ጥንካሬ ሳይሆን በተቃዋሚዎቹ ድክመትና ጥንካሬ ነው። ስለሆነም ከአሁን በኋላ የትግሉ ዋና ትኩረትና ርብርብ አገዛዙን በመተቸት ላይ ሳይሆን የራሱን ውስጣዊ ድክመቶች በሃቅና በድፍረት በመመርመርና በማረም ላይ መሆን አለበት።

በተለምዶ ሲባል እንደምንሰማው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው በመስቀለኛ ወይም በመንታ መንገድ ላይ አይደለም። ይልቁንም መዳረሻው “ምጽአተ-ኢትዮጵያ ” መሆኑ አስቀድሞ በታወቀ ነጠላ /One-way/ መንገድ ላይ ነው። ከዚህ “ምፅአተ-ኢትዮጵያ ” ሊባል ከሚችል ዘግናኝ አደጋ ሕዝብና አገርን ለመታደግ ከፈለግን ደፋር የእርምት እርምጃዎችን በራሳችን ላይ መውሰድ የግድ ይለናል። ተቃዋሚው ጎራ “ባንዳ፣ ጁንታ፣ ሸኔ ወይም ጃውሳ” ከሚል ተራ የቃላት መፈራረጅ ጀምሮ እስከ የጎንዮሽ የእርስ-በእርስ ግጭት ድረስ ያሉ ፈርጀ-ብዙ ድክመቶቹን ከውስጡ አራግፎ መጣል፤ ከዚያም እየተገዳደሉ ከመፈራረስ አደጋ ኢትዮጵያ ን የመታደግ ዓላማን ቀዳሚና ዋና የትግል አጀንዳው በማድረግ አገዛዙን በትብብር መታገል ይኖርበታል። የወቅቱ ትግል በዚህ መጠን ራሱን መለወጥ ካልቻለ በስተቀር፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ የሚገኘው የትጥቅ ትግልም ቢሆን፣ ቢበዛ መንግስትን ከማዳከምና ከማፍረስ ባለፈ አሁን ላይ እየተመኘን ያለነውን ዘላቂ ለውጥ በቅርብም ሆነ በሩቅ ጊዜ ሊያስገኝልን አይችልም።


ተመሳሳይ ርዕስ ለማንበብየዶላር እና የብር ወግ – ጥቂት ነጥቦች ስለ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ቅነሳ – በክቡር ገና 


መግቢያ

ይህንን “ባይዋጥልዎም እነሆ ፖለቲካ” የሚል ያልተለመደ ንዑስ ርዕስ ለዚህ መጣጥፍ የመረጥኩት ያለምክንያት አይደለም ። በዚህ መጣጥፍ ላይ ያሰፈርኳቸው አብዛኛዎቹ ሃሳቦች “እያበለጸግኋችሁ ነው” ለሚለን መንግስት ም ሆነ፣ “አገዛዙ አልቆለታል ” ለሚሉት ተቃዋሚ ኃይሎችም እንደማይዋጡ አስቀድሜ ስለምገነዘብ ነው። አንባቢም “ሃሳብህ ለመንግስትም ለተቃዋሚውም ወገን የማይዋጥ ከሆነ ችግሩ የአንተ ነውና ራስህን መርምር” ሊል እንደሚችል እገምታለሁ ። እውነት ነው፤ ራሴን እንደከሰረ ፖለቲከኛ
መቁጠርና በብሔርተኞችና በፅንፈኞች አሸናፊነት ስር በወደቀው የአገሪቱ “ፖለቲካ ተብዬ” የትግል ሂደት ውስጥ ያለኝን ሚና መመርመር ከጀመረኩ ቆይቻለሁ ።

በ27 ዓመቱ የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በፖለቲካ ጉዳይ ከሌሎች ጋር የመወያየት ወይም የመከራከር ቀጠሮ ካለኝ አንብቤና መረጃ አሰባስቤ ለመዘጋጀት እገደድ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ግን የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ ቧልት፣ ስድብ፣ ዛቻ፣ ብሽሽቅ፣ ጥላቻ፣ ብቀላ፣ የሃይማኖት ስብከት፣ እርግማንና ተረት-ተረት ስለቀየሩት የውይይትና የክርክር ዝግጅት ማድረግ ካቆምኩ እነሆ አምስት ዓመት ተኩል ሆነኝ።

በአገዛዝ ዘመናቸውም ስለዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር፣ የህገ-መንግሥት መሻሻል፣ ከድህነት መላቀቅ ወዘተ ሲደረግ የነበረውን ትግል እንደ አገርና ሕዝብ ወደ መኖርና ያለመኖር የህልውና ትግል አውርደውታል። በዚህም ምክንያት በፖሊሲ ጉዳዮች ወይም በርዕዮተ-ዓለም መነፅር ፖለቲካን ለማየት የምንሞክር ሰዎች በወቅቱ የብሽሽቅ፣ የጥላቻ፣ የተበዳይነት ፉክክርና የግጭት “ፖለቲካ” ውስጥ ባይተዋር ከሆንን ሰንብተናል ። በወቅቱ የብልጽግና ዘመን ጥሩ ፖለቲከኛ መሆን ማለት ጥሩ ተሳዳቢ፣ ጥሩ “ዘረኛ”፣ ጥሩ ጉረኛ ወይም ጥሩ ሙሾ አውራጅ መሆን ነውና የአንዳንዶቻችን ድካም አጉል “የቁራ ጩኸት” ከሆነ ቆይቷል።

የዛሬው መጣጥፌ በዋናነት የሚያተኩረው በተቃዋሚው ጎራ ላይ ይሆናል። በእኔ በኩል ተቃዋሚው ጎራ ውስጣዊ ድክመቶቹን ካልፈታ በስተቀር ትግሉ የትም እንደማይደርስ መገንዘብና ውስጣዊ ችግራችን እንዲፈታ መታገል የጀመርኩት ገና የመአሕድ የወጣት ክንፍ ሊቀመንበር በነበርኩበትና ድርጅቱን ወክዬ የ33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት በነበረው “በአማራጭ ኃይሎች” ምክር ቤት ውስጥ እሳተፍ ከነበረበት ከዛሬ 29 ዓመት ጀምሮ ነው። ኢዴፓ እንደ ፓርቲ፣ የሕዝቡ ትግል ለዘላቂ ውጤት መብቃት የሚችለው
አገዛዙን በመታገል ብቻ ሳይሆን በሕዝቡና በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ያሉና ለትግሉ መጠናከር እንቅፋት የሆኑ አሉታዊ አመለካከቶችን በመታገል ጭምር እንደሆነ በአደባባይ መናገርና መፃፍ ከጀመረም ከ23 ዓመት በላይ ሆኖታል።

እንደአለመታደል ሆኖ ግን ይህ የረዥም ጊዜ ጩኸታችን አሉቧልተኞች ስማችንን በአፍራሽነት ወይም በሰርጎ-ገብነት ለማጥፋት ለሚያደርጉት ጥረት ግብዓት ሆኖ አገለገለ እንጂ ውጤት ለማምጣት አልጠቀመም ። ጩኸታችን ሰሚ ባለማግኘቱም የአብዛኛው ሕዝብ ድጋፍ ያልነበረው አምባገነኑ ኢህአዴግ 33 ዓመት በስልጣን ላይ የመቀጠል ዕድል አግኝቷል ። ከዚህ ሁሉ ውድቀት በኋላም ተቃዋሚው ጎራ ግልፅ ከሆነው ስህተቱ መማር ባለመቻሉ ዛሬም እንደትናንቱ የአገሪቱ የመፍትሄ ሳይሆን የጥፋት አካል ሆኖ ቀጥሏል። ከዚህ የድክመት አዙሪት ሰብሮ የመውጣት አስፈላጊነት ፈፅሞ አልታይህ ብሎት በተለመደው መንገድ እየተጓዘ፣ ግን ደግሞ የተለየ ውጤት እየጠበቀ መቀጠልን መርጧል።

በእኔ በኩል በአሁኑ ወቅት እንዲህ የምጽፈውም ሆነ የምናገረው ፣ ሃሳቤ በስፋት እና በብዛት ሊደመጥ ወይም ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል የሚል አጉል ተስፋ ኖሮኝ አይደለም ። ይልቁንም ሕዝቡ በጦርነት እያለቀና አገሪቱ በመፈራረስ ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት “ተስፋ ቆርጠህ ዝም አትበል፤ የሚሰማህንና ያመንክበትን ሁሉ ተናገር” የሚለውን የጥቂት የፖለቲካ አመለካከት ተጋሪዎቼንና የራሴን እንቅልፍ የሚነሳ የሞራል ጥያቄ ለመመለስ ስል ነው።

በዚህ ዓይነቱ ጨለምተኛ ስሜት ውስጥ ሆኜ የፃፍኩት የዛሬው መጣጥፌ በጥቅሉ – “በወቅቱ ትግል ተቃዋሚ ኃይሎች በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን ? በያዝነው መንገድ መጓዝ ከቀጠልን መዳረሻችን የት ይሆናል? ዘላቂና ተፈላጊ ለውጥ ለማምጣት ከፈለግንስ ምን ማድረግ ይገባናል?” ለሚሉት ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መሞከር ይሆናል። በመግቢያ ዬ ላይ እንዳልኩት፣ ባይዋጥልዎም
ያንብቡት።

I. የተቃውሞ ትግሉ የት ላይ ነው የሚገኘው ?

ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት የህልም ዓለም በሚመስል ሁኔታ የገዥው ፓርቲ፣ የመንግሥ ትና የሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚው ጎራም መሪ ሆነው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሁን ላይ ልጅ-አዋቂው ሲዘባበትባቸው፣ ሲቀልድባቸው ፣ ሲረግማቸውና ሲቃወማቸው የሚውል የተናቁና የተጠሉ መሪ ሆነዋል። ብዙ ውድመትና እልቂት በአገርና በሕዝብ ላይ ከደረሰ በኋላም ቢሆን አብዛኛው ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሙሴነት” ወይም አሻጋሪነት ተስፋ ቆርጧል። በየፌርማታው እየተንጠባጠበም ቢሆን አብዛኛው ተደማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ሆኗል። እርግጥ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ነን የሚሉ ጥቂቶች ዛሬም አሉ። እነዚህ ጥቂቶች ግን ራሳቸውን ካልዋሹ በስተቀር የአገዛዙ የስልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ተጋሪዎች፣ አሊያም ፖለቲካን የመረዳት አቅማቸው እጅግ ዝቅተኛና ደካማ ስለሆነ እንጂ ድጋፋቸው ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ጋር የሚያያይዘው ሌላ ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት ኖሮት አይደለም ።

የሕዝቡ የቀድሞው ጭፍን ድጋፍም ሆነ የአሁኑ የጅምላ ተቃውሞ በአብዛኛው በሃሳብ አንድነትና በጠራ መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም ። የቀድሞው ጭፍን ድጋፋችን “ህዝባዊ ስካር” ሊባል በሚችል መጠን የጎራ መደበላለቅ የነበረበትና ያልተገባ ጥላቻ ውስጥ ገብተን የሰራነው ስህተት ነው። የአሁኑ የጅምላ ተቃውሞአችንም ወጥ የሆነ ምክንያት ያለውና የጠራ መርህን የተከተለ አይደለም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ን “የአሃዳዊነት ወኪል ናቸው” ብለው ከሚተቹት ንዑስ ብሔርተኞች ጀምሮ፣ “የኦሮሙማ አቋም አራማጅ ናቸው” ብለው እስከሚቃወሟቸው አገራዊ ብሔርተኞች ድረስ ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ ላይ ተጃምለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ሆነዋል። እንደዚህ ያለ ተቃራኒ አቋም ይዘው የጅምላ ተቃዋሚ ከሆኑት ኃይሎች ውስጥ የትኛው አሸናፊ ሲሆን አገሪቱን ከህልውና ጥፋት እንደሚታደጋት ግልፅ የሆነ መግባባት የለም። እንዲህ አይነቱ ጥያቄ ግልፅ እንዲሆን የሚያስችል ውይይት እንዲካሄድም በወቅቱ ፖለቲካ አይፈለግም ። ይሁንና አሁን ላይ አብዛኛው ሕዝብ የአገዛዙ ተቃዋሚ ሲሆን ቀላል የማይባል ሕዝብም እንደተለመደው አገዛዙን ለማስወገድ እየታገለና መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል።

ሕዝቡ በዚህ መጠን በየራሱ ጉራማይሌ የሆነ ምክንያት “አገዛዙ አይበጀኝም ” ብሎ ለትግል መነሳሳቱ ለትግሉ መጠናከር አንድ አስፈላጊ ቅደመ-ሁኔታ ነውና “ይበጅ” የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ “አገዛዙ አልቆለታል፤ የምንፈልገው ለውጥ ሊመጣ ተቃርቧል ” የሚል አመለካከት በተቃዋሚው ጎራና በሕዝቡ ውስጥ በሰፊው ተፈጥሯል ። አንዳንድ ስሜታዊ የሆኑ ማህበራዊ አንቂዎች (እኔ “ማህበራዊ አደንቋሪዎች ” የምላቸው ) እና ተስፈኛ ፖለቲከኞችም “የአገዛዙ ግብዓተ-መሬት በቅርቡ ይፈጸማል፤ የወቅቱ ጭንቀታችን ድህረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ትሁን? የሚል ነው” በማለትም የተጋነነ ተስፋ ለሕዝብ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ ።

በእኔ በኩል በእንዲህ አይነቱ ሃሳብ እምብዛም አልስማማም ። ስለ ድህረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ ከወዲሁ ማሰብ መቻል የማይጠላ ቁም ነገር ቢሆንም፣ አሁን ላይ በያዝነው በብዙ ድክመቶችና ችግሮች የተሞላ የትግል አካሄድ ከቀጠልን ግን – አንደኛ፣ አገዛዙን አሁን ላይ እንደሚታሰበው በቀላሉና በአጭር ጊዜ ከስልጣን ማስወገድ አንችልም፤ ሁለተኛ፣ በራሱ ውስጣዊ ምክንያት ወይም በትግሉ በሚከፈል ከፍተኛ መስዋዕትነት አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድ ከተቻለም ድህረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ በህልውና የመቀጠል ዕድሏ እጅግ ጠባብ ይሆናል እላለሁ።

አንድ ሕዝብ አንድን በስልጣን ላይ የሚገኝ አገዛዝ ስለጠላውና ስለተቃወመው፣ ከመቃወምም አልፎ ስለታገለና መስዋዕትነት ስለከፈለ ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ማለት አይቻልም ። መቃወም፣ መታገልና መስዋዕትነት መክፈል በራሱ የውጤት ዋስትና ቢሆን ኖሮ በፖለቲካ ትግል ታሪካችን ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸው የሕዝብ ትግሎች በተደጋጋሚ በሌሎች ሲጠለፉና ሲከሽፉ ባልታየ ነበር። እንዳለፉት የከሸፉ የትግል ሂደቶች ሁሉ የወቅቱ ትግልም “ከአሁን በፊት የተካሄዱ የሕዝብ ትግሎች ለምን በተደጋጋሚ ከሸፉ? የወቅቱ ትግል ተመሳሳይ አደጋ እንዳይገጥመው ስ ምን መደረግ አለበት?” በሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ተገቢ ትምህርት ያልወሰደ፣ ለመውሰድ የሚደረግን ሙከራም ሁሉ አፍራሽነትና ነውር አድርጎ የሚያይ ነው። ስለሆነም የወቅቱ ትግልም ከተመሳሳይ አደጋ የመዳን ዋስትና አለው ማለት አይቻልም ። በእርግጥ የቀደሙ የለውጥ ዕድሎችን ያከሸፉ በርካታ ሰዎች የዛሬውንም ትግል በበላይነት ስለተቆጣጠሩት ይህ መሆኑ የማይጠበቅ አይደለም ።

ቢያንስ በአለፉት 60 ዓመታት በተደጋጋሚ በክሽፈት ላመለጡን የለውጥ ዕድሎች ምክንያት የሆኑት ድክመቶችና ችግሮች በዛሬው የትግል ሂደትም በብዙ መጠን አሉ። እንዲያውም በቀድሞዎቹ የትግል ሂደቶች ያልነበሩ በርካታ አዳዲስ ድክመቶችና ችግሮች በአሁኑ የትግል ሂደት ላይ በብዛት ተጨምረዋል ።

በትናንቱም ሆነ በዛሬው የትግል ሂደት በወጥነት የነበሩትና ያሉት ድክመቶች በጥቅሉ ሦስት ናቸው ማለት ይቻላል። እነርሱም፡ –

አንደኛ፡- ትግሉ በሕዝቡ ውስጥ የጎላ ማህበራዊ መሰረት ባለው ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አለመመራቱ፤

ሁለተኛ፡- በትግሉ ሂደት ውስጥ ያሉና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንወክላለን የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች (ቢያንስ) በመለስተኛ የጋራ ፕሮግራም መሰባሰብና አገዛዝን በጋራ መታገል አለመቻላቸው ፤

ሦስተኛ፡- ተቃዋሚ ኃይሎች ከስልጣን ስለሚያወርዱት እንጂ ስለሚተኩት ስርዓት ምንነት ተጨንቀው ተገቢ ዝግጅት አለማድረጋቸው ነው፡፡ ይህ ማለትም በአግባቡ የተጠና እና የተተነተነ፣ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በአግባቡ የሚያቻችል እና የሚፈታ፣  የትግሉ ባለቤት የሆነውን ሕዝብም ሆነ የውጭ መንግሥታትን በብቃት ሊያሳምን የሚችል አማራጭ ሃሳብ ይዞ አለመቅረብ ዋና ዋናዎቹ ድክመቶች ናቸው።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ወጥ ድክመቶች አለመፈታታቸው ለትግሉ ውጤታማ አለመሆን ዋና ተግዳሮት መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ትግሉን ከመፍትሄው የበለጠ የሚያርቁና በወቅቱ የትግል ሂደት ላይ የተጨመሩት የሚከተሉት አዳዲስ ድክመቶችና ችግሮች ደግሞ በጥቅሉ ስድስት ናቸው ማለት ይቻላል። እነርሱም፡ –

አንደኛ፡- የጋራ ማንነታችን መገለጫ የሆኑት ሰውነትና ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቦታና ዋጋ ያጡበት፣ ልዩነትን ብቻ መሰረት ያደረገና ወደ ዘረኝነት የተጠጋ ብሔርተኝነት ብቸኛ የመደራጃና የመታገያ ስልት መሆኑ፤

ሁለተኛ፡- ለዘላቂ ለውጥ ሊያበቃን የሚችለው የሠላማዊ ትግል ስልት ተንቆና ተጠልቶ ለዘመናት ዋጋ ሲያስከፍለን የኖረው ኋላ-ቀር የጦርነት ስልት እንደገና ብቸኛ የመታገያ አማራጭ መሆኑ፤

ሦስተኛ፡- ፖለቲካና ኃይማኖት ቅጥ-ባጣ መጠን መደበላለቁ ፤

አራተኛ፡- ፖለቲካ ፖሊሲ ነክ አጀንዳዎችንና ርዕዮት-ዓለምን መሰረት ያደረገ የሕዝብ አስተዳደር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የታሪክ ክርክር፣ የጦረኝነት ፉክክር፣ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ፣ የተበዳይነትና የተጠቂነት ፉክክር መድረክ መሆኑ፤

አምስተኛ፡ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳሉ በማይቆጠርበት መጠን ደካማና የተከፋፈሉ ከመሆናቸውም  በላይ በጎንዮሽ ትግል እርስ-በርስ የሚናቆሩና የሚገዳደሉበት፣ ችግሩ ከፖለቲካ ኃይሎች አልፎ “የሕዝብ-ለሕዝብ” የመሆን አዝማሚያ መያዙ፤

ስድስተኛ፡ የተቃውሞ ትግሉ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሲቪክ ማህበራት ሳይሆን በዋናነት ስሜታዊ፣ ፅንፈኛ፣ “ዘረኛ” ወይም ጥቅመኛ በሆኑ አክቲቪስቶችና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚመራ መሆኑ ናቸው።

II. ትግሉ ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ መዳረሻው የት ይሆናል?

የወቅቱ ትግል እነዚህን ቀድመው የነበሩና በአዲስ መልክ የተፈጠሩ መሰረታዊ ድክመቶችና ችግሮች በወሳኝ መጠን እስካላስወገደ ድረስ ወደፊት ሊጠብቀን የሚችለው ከሚከተሉት ሁለት ውጤቶች መካከል አንደኛው ይሆናል።

ውጤት 1

ብዙ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ በቀላሉ ከስልጣን መወገድ እንደሚችል አድርገው የሚያስቡት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ድክመቶች በመነሳት፣ አሊያም አማፂያን በተለያዩ ክልሎች የሚያካሂዱት ጦርነት የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ከሚል ተስፋ በመነጨ ሲሆን ይታያል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቃላቸው የማይታመኑ ዋሾ፣ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨትና በማጋደል እጠቀማለሁ ብለው የሚያስቡ ጦረኛ፣ አገርን የማስተዳደር ልምድና ዕውቀት የሌላቸው ደካማ መሪ መሆናቸውን ሕዝቡ ጠንቅቆ ስላወቀና ስለተቃወመ ብቻ የአገዛዙ ዕድሜ ያጥራል ብሎ በርግጠኝነት መናገር ስህተት ይሆናል። በተለያዩ ክልሎች ጦርነት ስለተቀጣጠለም የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ብሎ እርግጠኛ መሆን ከራስም ሆነ ከሌሎች አገሮች ታሪክ አለመማር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ዕውቀት፣ ልምድና ቅንነት የሌላቸው ቢሆንም በየትኛውም መንገድ ስልጣንን አስጠብቆ በማስቀጠል ረገድ ያላቸው አቅምና ብቃት ግን የሚናቅና የሚካድ አይደለም ። ኢትዮጵያን በመሰለ ኋላ-ቀር አገር ዋናው የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ገደብ-የለሽ በሆነ መጠን ፈሪና ጨካኝ መሆን፣ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ ራስን አብልጦ መውደድ፣ ከማንም በላይ እኔ ሁሉን አዋቂ ነኝ ብሎ ለማስመሰል መድፈር፣ የከፋፋይነት ሴራን የተካኑ መሆን፣ የመንግሥት ሹመትንና የኢኮኖሚ ጥቅምን ለአድርባዮች ና ለአገልጋዮች በለጋስነት የማከፋፈል ብቃት መኖር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው ብቃትና ችሎታ ደግሞ ብዙዎች ከምንገምተው በላይ እጅግ የረቀቀና የሰላ ነው።

የመሪነት የስራ ድርሻቸውን የሕዝብ ሠላምና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ የአገር ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ ልማትን ማስፋፋትና ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠርን ሳይሆን ሕዝብን እያደኸዩና እርስ-በርሱ እያጋደሉ የስልጣን ዕድሜን ማራዘም ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይህ አሉታዊ ብቃታቸው በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ካሉ መሰረታዊ ድክመቶች ጋር ተዳምሮ ከግምታችን ውጭ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድል ሊፈጥርላቸው ይችላል። በአገራችንም ሆነ በሌሎች ኋላ-ቀር አገሮች በእጅጉ የተጠሉና የተናቁ መሪዎች ለብዙ አስርት ዓመታት እንደዋዛ በስልጣን ላይ ሲቆዩ አይተናል። ይህ ሁኔታ ዛሬም በአገራችን አይደገምም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ግብዝነት ይሆናል።

ወደኋላ መለስ ብለን ለማስታወስ ብንሞክር፣ በ1953 ዓ.ምህረቱ መፈንቅለ መንግሥት አልጋው ተነቃንቋል ና ዕድሜ አይኖረውም የተባለው የንጉሱ ስርዓት ከዚያ በኋላ ንጉሱ በእርጅና ጃጅተው አካባቢያቸው ን መቆጣጠር እስከተሳናቸው ጊዜ ድረስ ለ14 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይቷል። የፖለቲካ መሃይም ነውና ከአንድ ዓመት ያለፈ ተረጋግቶ በስልጣን ላይ መቀጠል አይችልም ተብሎ ይናቅ የነበረው ወታደራዊው ደርግም በጠብመንጃና በአብዮታዊ መፈክር ለ17 ዓመታት ገዝቶናል። ተራ ሽምቅ ተዋጊና ‘ተገንጣይ-አስገንጣይ ’ ነው ተብሎ ይጠላ የነበረው ኢህአዴግ ም ለ27 ዓመታት አንቀጥቅጦ ገዝቶናል። ይህ ሁሉ የሆነው በወቅቱ ከነበረው የሕዝብ ፍላጎትና ግምት ውጭ ነበር።

አሁንም ምንም ዓይነት የትግል መሪነት ታሪክ የሌላቸው፣ እንኳንስ ትልቅ አገርን አንድን ወረዳ ለማስተዳደር የሚያስችል እውቀትና ብቃት የሌላቸው፣ ትናንት የተናሩትን ዛሬ የመድገም ስብዕና የሌላቸው፣ ለስልጣን ከበቁበት አንድ ዓመት በፊት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን የማያውቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አፍዝዘውና አደንግዘው ለአምስት ዓመት ተኩል እንደገዙን ሁሉ ወደፊትም ለሌላ አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ ቀጥለው እንደ ደርግና ኢህአዴግ ሊያስገርሙንና ሊያስደምሙን እንደማይችሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ። የጀመሩትን ውድና ቅንጡ ቤተ- መንግስታቸውን እንደተመኙት ጨርሰው ሊኖሩበት ም ይችሉ ይሆናል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችም የሚፈለገውን ለውጥና ውጤት እንደሚያመጡ አድርጎ በእርግጠኝነት ማሰብ ቢያንስ በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ስህተት ነው። አንደኛ፣ ጦርነት በስልጣን ላይ ያለን አገዛዝ ከማዳከምና ከማፍረስ ባለፈ ዘላቂ ለውጥ እንደማያመጣ የአገራችን ም ሆነ የሌሎች አገሮች ተደጋጋሚ ተሞክሮ ማሳየቱ፤ ሁለተኛ፣ ከላይ ከፍ ሲል የተዘረዘሩትና በትግሉ ዙሪያ የሚታዩ ዘጠኝ ነባርና አዳዲስ ድክመቶች አስተማማኝ በሆነ መጠን ካልተፈቱ በስተቀር የወቅቱ የትጥቅ ትግል የአገሪቱን የመፍረስ ሂደት ከማባባስና አይቀሬ ከማድረግ ባለፈ የምንመኘውን በጎ ለውጥ ሊያስገኝልን አለመቻሉ ናቸው።

እዚህ ላይ ጦርነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይፈልጉትና ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት የመጣባቸው ችግር ሳይሆን ለስልጣናቸው መራዘም ይጠቅመኛል ብለው በማሰብ ራሳቸው ሆን ብለው የሚያራምዱት ቋሚ የአገዛዝ ፖሊሲያቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ። ለእርሳቸውና አገዛዛቸው የሚከብዳቸው፣ የሚያሰጋቸውና አምርሮ የሚያስፈራቸው፣ ለሕዝቡ ትግልም አዋጪና ተገቢ የሚሆነው ጦርነት ሳይሆን ሠላማዊ ትግል ነው። ብዙዎች ይህንን ሃሳብ በቀላሉ ለመግዛት እንደሚቸገሩ ባውቅም እኔ ግን ይህንን የምለው ከግምትም በላይ በሆነ እርግጠኛነት ነው።

የሚበጀንን በአግባቡ መገንዘብና መምረጥ ተስኖን እንጂ ጦርነት ከሚያስከፍለን በብዙ እጅ ባነሰና በቀለለ ዋጋ ሠላማዊ ትግል ለዘላቂ ውጤትና ድል ባበቃን ነበር። የወጣቶች ህይወት ከቁጥር ያለፈ ዋጋና ትርጉም ባጣበት በዛሬዋ አገራችን በሁለት ዓመት ጦርነት ብቻ ከሚሊዮን በላይ ዜጎቻችንን ህይወት አጥተናል። አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ከጦርነት ይልቅ ለሠላማዊ ትግል ቆርጦ ቢሰለፍ አገዛዞች በጉልበት እየገዙን ለመቀጠል የቀናት ወይም የሳምንታት ዕድሜ ባላገኙ ነበር።

አገዛዙ ‘ጦርነትን የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍን’ በዓይን-አውጣነት ሲከለክልና ሠልፍ ጠሪዎችን በጅምላ ሲያስር የተመለከት ነው፤ ታዬ ደንደአ ጦርነትን መቃወም ሲጀምር ሳይውል ሳያድር ወደ ወህኒ ሲጋዝ ያየነው ያለ ምክንያት ሳይሆን የአገዛዙ ዋና ደካማ ጎን ሠላማዊ ትግልን መቋቋም አለመቻል ስለሆነ ነው። አገዛዙ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ሆን ብሎ ሲሰራ የኖረው ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ ጦርነት አማራጭ እንዲገባ ለማድረግ ነው። እኛም ሠላማዊ ትግል አያዋጣም ብለን ወደ ጦርነት አማራጭ የገባነው በእርግጥም አገዛዙ ያጠመደልን ወጥመድ ውስጥ ስለወደቅን ነው። ከሁሉም በላይ የአንድ አገዛዝ በስልጣን ላይ የመቀጠል ዕድል በዋናነት የሚወሰነው በራሱ ጥናካሬና ድክመት ሳይሆን በተቃዋሚዎቹ ጥንካሬና ድክመት ነው። ይህንን በውል መገንዘብ ካልቻልን ከፊታችን የሚጠብቀን ውጤት ከምንገምተው ውጪ “የአገዛዙ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ መቆየት” ሊሆን ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ አስከ ቆዩ ድረስም አገሪቱ የበለጠ እየደኸየችና የእርስ-በርስ ጦርነቱም የበለጠ እየተባባሰ ስለሚመጣ ድህረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ በህልውና የመቀጠል ዕድሏ እጅግ ጠባብ ይሆናል።

ውጤት 2

ከለውጥ መምጣት ጋር በተያያዘ የወቅቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመን ከአለፉት የአገዛዝ ስርዓቶች በዋናነት የተለየና የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው አንድ ጉዳይ ነው። እርሱም ስለ ለውጥ ሲታሰብ በቀድሞዎቹ አገዛዞች ዘመን የነበረው ዋና ጭንቀት “ከአገዛዙ ውድቀት በኋላ የባሰ ስርዓት ይመጣብን ይሆን?” የሚል ሲሆን፣ በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመን የገጠመን ዋና ጭንቀት ግን “ከእሳቸው ውድቀት በኋላ ድህረ-ዐቢይ የምትባል ኢትዮጵያ ትኖር ይሆን?” የሚል መሆኑ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕዝብን እርስ-በርስ ማዋጋትና ማደኽየትን “ዋና የአገዛዝ ፖሊሲያቸው ” አድርገው የሚያዩና አገሪቱ ለየትኛውም ዓይነት ከፍተኛ የህልውና አደጋ ብትጋለጥ ስልጣን መልቀቅን ፈጽሞ አማራጭ አድርገው ማሰብ የማይችሉ ግብዝ መሪ ናቸው። ምናልባትም ኮሎኔል መንግሥቱ ቃል ገብተው ማድረግ ሳይችሉት የቀሩትን “አንድ ሰው እስኪቀር እንዋጋለን ” የሚለውን መፈክር እንደ ጀብደኛው የታሚል ታይገርስ መሪ ቬሉፒላይ ፕራብሃካራን (Velupillai Prabhakaran) በተግባር ሊያውሉ የሚችሉ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብቻ ይመስሉኛል ። ሚሊዮኖች በተራቡበት አገር ድሮን ሲገዙና ቅንጡ ቤተ-መንግሥት ሲገነቡ፣ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ ዜጎችን በግፍ ሲያስሩ ከሚውሉና በቅዠት ዓለም ውስጥ ካሉ መሪ የጥፋት ተልዕኮ አገሪቱ ተርፋ በህልውና ልትቀጥል ትችላለች ብሎ ማሰብ መብት ቢሆንም አሳማኝ በሆነ የፖለቲካ አመክንዮ ሊደገፍ የሚችል አስተሳሰብ አይደለም ።

በእኔ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደጋጋሚ በግል አውርቼ፣ እንደማንኛውም ዜጋም የአደባባይ ንግግራቸውንና ተግባራቸውን በጥልቀት ገምግሜ የደረስኩበት ድምዳሜ (የባለሞያ አባባል ባልሆነ ተራ አነጋገር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃውሞን፣ አደጋንና ሃዘንን ለመረዳት የሚያስችለው የአንጎላቸው ክፍል ቀድሞውኑም አልተፈጠረም፣ አሊያም በሆነ አደጋ “የወለቀ” መሆኑን ነው።

እንደ ተቃዋሚው ጎራ ሁሉ የወቅቱ አገዛዝም ከአለፉት አገዛዞች በብዙ ርቀት በተለየና በባሰ ሁኔታ በብዙ መሰረታዊ ድክመቶች የተሞላ ነው። በዚህም ምክንያት አገዛዙ በውጫዊ የሕዝብ ትግል ጫና ብቻ ሳይሆን በራሱ ውስጣዊ ችግርም (በመፈንቅ ለ መንግሥት ም ሊሆን ይችላል)፣ በማናቸውም ባልታሰበ ቅርብ ጊዜ (ነገም ሊሆን ይችላል) በድንገት ሊፈረካከስ ይችላል። ይህን መሰል ድንገተኛ ሁነት ከተከሰተም አገሪቱ የሚገጥማት ዕጣ-ፈንታ በሌላ የተሻለ ወይም የባሰ መንግሥት የመገዛት ሳይሆን ጭራሹን መንግሥት -የለሽ መሆን ሊሆን ይችላል።

እንዲህ አይነቱ አደጋም መንግሥት -የለሽ በመሆን፣ ወይም ወደ ሦስትና አራት አገራት በመከፋፈል ብቻ የማይገለፅና የማይቆም፤ ምን አልባትም በአገራችንም ሆነ በዓለማችን የእርስ-በርስ ጦርነት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ና “ምጽዓተ-ኢትዮጵያ” በሚባል መጠን ለብዙ አስርት ሚሊዮን ዜጎች እልቂትና ስደት ሊዳርገን፤ እንደ ሕዝብም ህልውናችን ን አስከወዲያኛ ው ሊያጠፋው፣ ተመልሰን ም አገር የመሆን ዕድል ላያስገኝልን ይችላል። አሁን ላይ የደረስንበት የጥላቻ መጠንና እያሳየን ያለነው በጭካኔ የመገዳደል ደረጃ የሚጠቁመው ወደዚህ ዓይነቱ አስከፊ ሁኔታ የመግባት ዕድላችን ሰፊ መሆኑን ነው።

በሕዝብና በአገዛዙ መካከል ብቻ ሳይሆን አንዱ ተቃዋሚ ከሌላው ተቃዋሚ ጋር የተጓዳኝ ትግል ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ አገዛዙ በራሱ የውስጥ ችግር ምክንያት ቢፈረካከስ አገሪቱ አብራ የመፍረስ ዕድሏ ሰፊ ነው። በተቃዋሚው ጎራ ድክመት ምክንያት አገዛዙ በስልጣን ላይ የመቀጠል የበለጠ ዕድሜ ካገኘም የአገሪቱ መፍረስ የበለጠ አይቀሬ ይሆናል። ችግራችንን የበለጠ ውስብስብና ከባድ ያደረገው በእንዲህ ዓይነቱ ዙሪያው ገደል የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ መሆናችን ነው።

ችግሩን በዚህ መጠን የተረዳ ጥሩ የአገር መሪና መንግስት፣ ወይም አገዛዙ ለሃቀኛ ድርድር እንዲቀመጥ ለማስገደድ አሊያም አሸንፎ ለመተካት የሚችል ጠንካራ የተቃዋሚ ጎራ ካላገኘን በስተቀር “ከምጽአተ- ኢትዮጵያ ” በቀላሉ ልንተርፍ አንችልም ። ስለዚህ አገዛዙን መቃወምና መታገል ብቻውን በራሱ ለዘላቂ ውጤት አያበቃንም። አገዛዙን ለድርድር ለማስገደድ፣ ወይም ከስልጣን ለማስወገድም ሆነ አገዛዙ ሲፈርስ አገሪቱ አብራ እንዳትፈርስ ለማድረግ ፣ የተቃዋሚው ጎራ ችግሮቹን ፈትቶ መጠናከር መቻሉ ምትክ የሌለው ቅድመ ሁኔታ ነው።

III. እየተገዳደሉ ከመፍረስ ለመዳን ምን ይደረግ?

ብዙዎቻችን ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ የሚመሩትን አገዛዝ እየተቃወምን የምንገኘው በየራሳችን በተቃርኖ የተሞላ ምክንያት ነው። ይህ ተቃርኖ የትግሉን የወደፊት ውጤት በመወሰን ረገድ የራሱ አሉታዊ ሚና ያለው ቢሆንም ቢያንስ አገዛዙ ለሁላችንም እንደማይጠቅም ግን አሁን ላይ አብዛኛው ሕዝብ ተገንዝቧል ። ስለሆነም ከእንግዲህ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆነ ስለአገዛዛቸው ማንነትና ባህሪ የምናውቀው ና የምናጋልጠው አዲስ ነገር ስለማይኖር እነሱ ስለሚፈጽሙት ጥፋትና ወንጀል በየእለቱ እያወሩ ከመዋል ይልቅ ዋናው ትኩረታችን በራሳችን ዙሪያ ባሉ ድክመቶችና ችግሮች ላይ መሆን ይኖርበታል ። ከሁሉም በላይ ትግሉን ለዘላቂ ውጤት ሊያበቃው የሚችለው ቀዳሚ ውሳኔ ተቃዋሚው ጎራ ስለራሱ ውስጣዊ ሁኔታ የሚያደርገው ግምገማ ነው። የተቃዋሚው ጎራ እጅግ ደካማና በብዙ ችግሮች የተሞላ መሆኑን ከልብ አምኖ በመቀበል በራሱ ላይ ደፋርና ሃቀኛ ግምገማ አካሂዶ ያሉበትን ድክመቶች ትርጉም ባለው መጠን ማስወገድ አለበት። ይህን ማድረግ እስካልቻለ ድረስ ግን አገዛዙን ለድርድር ማስገደድ፣
ወይም በቀላሉ ከስልጣን ማስወገድም ሆነ አገሪቱንና ሕዝቡን ከህልውና ጥፋት ማዳን አይቻልም ። ይህንን እውነታ በቅድሚያ ና በድፍረት አምነን በመቀበል ትግሉን ለዘላቂ ውጤታማነት ለማብቃት የሚከተሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች መተግበር አስፈላጊ ይሆናል።

  1. እንደ ዜጋ፣ እንደ ብሔርም ሆነ እንደ ሕዝብ የህልውና ደህንነት ዋስትና ሊኖረን የሚችለው አገራዊ ህልውናችን ከነድክመቶቹም ጭምር መቀጠል ሲችል ብቻ ነው። ስለሆነም የትግላችን ቀዳሚ የጋራ ትኩረት የአገሪቱን ህልውና ከመፍረስ በማዳን ዓላማ ላይ መሆን አለበት።
  2. በታሪካችን ከበቂ በላይ ደጋግመን እንዳየነው በጦርነት ትግል ማናችንም በዘላቂነት አሸናፊ መሆን አንችልም ። ስለሆነም ሠላማዊ ትግል ለዘላቂ ውጤት የሚያበቃን ተገቢ፣ አዋጪና አስተማማኝ የትግል ስልት መሆኑ ሊታመንና ቀዳሚ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል።
  3. በአገዛዙ አስገዳጅ ባህሪ የተነሳ የትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ ኃይሎች የእርስ-በርስ የጎንዮሽ ግጭትንና ጦርነትን ማስወገድ፤ ከዚህም በላይ እንደ ሕዝብና አገር እየተገዳደሉ ከመፈራፈረስ መዳንን ማዕከል ባደረገ የጋራ አጀንዳ ዙሪያ በመሰባሰብ አገዛዙን በትብብር መታገል ይገባቸዋል ።
  4. ያለፈ ታሪክን፣ የጥፋትና የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ የሚታየው የወቅቱ የተካረረ ውዝግብ ለጊዜው ሊቆም ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ በቀላሉ መግባባት ላይ ሊደረስበት የማይችል ውዝግብ ለትግሉ ውጤታማነት እንቅፋት ስለሚሆን አገሪቱ ከህልውና አደጋ መትረፏ ከተረጋገጠ በኋላ ወደፊት ለሚካሄድ የብሔራዊ መግባባት እና የሽግግር ጊዜ ፍትህ ሂደት እንዲቆይ መደረግ አለበት።
  5. በአገሪቱ በሠላማዊ መንግድም ሆነ በጦርነት ትግል እያደረጉ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች የራሳቸውንም ሆነ የምልዐተ-ሕዝቡን ጥቅምና ህልውና ለሚያስከብር ና ገዢውን ፓርቲ “ሁሉን አቀፍና ሃቀኛ” ለሆነ ድርድር ማስገደድ የሚያስችል የድርጅትና የአጀንዳ ዝግጅት በአስቸኳይ ማድረግ ይኖርባቸዋል ። ችግሮችን በጠብመንጃ ኃይል ብቻ እፈታለሁ ብሎ የሚያምንን አገዛዝ በሕዝብ ትግል አስገድዶ በድርድር ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጥ ማድረግ ድል እንጂ ሽንፈት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
  6. የአገሪቱ ህልውና ከመፍረስ ተርፎ ልዩነቶችን በዴሞክራሲና ሠላማዊ በሆነ አግባብ ለመፍታት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የፖለቲካ ኃይሎች የሚያነሷቸው የማንነት፣ የወሰን፣ የአከላለል፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰንና ሌሎች ህገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ለጊዜው ወደ ጎን ሊቀመጡ ይገባል። በተለይም አዲስ አበባን፣ ድሬዳዋን፣ ወልቃይትንና ራያን ስለመሳሰሉ አካባቢዎች ያሉ ውዝግቦችና ክልል የመሆን ጥያቄዎች በአገር ደረጃ ከሚመጣ መዋቅራዊ መፍትሄ ተነጥለው አሁን በስራ ላይ ባለው ህገ- መንግሥታዊ ማዕቀፍ በቀላሉ ሊፈቱ እንደማይችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል ። ስለሆነም እነዚህ ጥያቄዎች አገዛዙ ተቃዋሚዎችን እየከፋፈለ ዕድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች እንዳይሆኑ ማድረግ ከተፈለገ ከእነዚህ አጀንዳዎች በፊት ቀዳሚው የጋራ ጥያቄ ሁሉን አቀፍና ሃቀኛ የሆነ አዲስ የሽግግር ሂደት መፍጠር ሊሆን ይገባል።
  7.  የፖለቲካ ትግሉ ስሜታዊ፣ ሴረኛ፣ ጽንፈኛ፣ “ዘረኛ’’ እና የደም ነጋዴ በሆኑ አክቲቪስቶችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይሆን ስትራቴጂክ አስተሳሰብና በጎ ስብዕና ባላቸው የፖለቲካ ሰዎችና ድርጅቶች መመራት አለበት። በእስካሁኑ የትግል ሂደት አሸናፊ መሆን ያልቻልን እኔን መሰል ፖለቲከኞች ም በወቅቱ ትግል የሚኖረን ተሳትፎ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከአመራርነት ሚና ልንገለልና አዲሱ ትውልድ የራሱን ዘመን ትግል በራሱ የመምራትና የመወሰን ዕድል እንዲያገኝ መደረግ አለበት።
  8. ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ልቦናና ወኔ አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነጠቁትን ስልጣን መልሶ በእጁ ማስገባት ከቻለና ተቃውሞን በኃይል አማራጭ የማፈን አቋሙን ቀይሮ ራሱን ለሃቀኛና ሁሉን አቀፍ ድርድር የሚያቀርብ ከሆነም በተቃዋሚው ጎራ ዘንድ የችግራችን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ የአገሪቱ የመፍትሄ አካልም ተደርጎ ሊታይ ይገባል።
  9. የወቅቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝና መከላከያ ሠራዊቱን የኦሮሞ መንግሥትና ሠራዊት አድርጎ ማየት ስህተት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍረጃ አገዛዙን ከመጥቀም ባለፈ እውነት ያልሆነና ከትግል ስልትም አንፃር ስህተት በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። “ባንዳ፣ ሸኔ፣ ጁንታ፣ ጃውሳ ወዘተ” የሚሉት ፍረጃዎችም ስህተትና የአገዛዙ የመከፋፈያ መሳሪያዎች ስለሆኑ ሊቆሙ ይገባል።
  10. አገዛዙም ሆነ አገሪቱ ዕድሜ አግኝተው ምርጫ 2019 ሊካሄድ ይችላል። ተቃዋሚዎች ያንን የምርጫ ዕድል በዋዛ ካሳለፉት ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ እንደሰራናቸው ስህተቶች ሁሉ ታሪካዊ ስህተት እንደሚሆን በማመን ለምርጫው ራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል ። በዚያ የ2019 ዓ.ም. ምርጫ ፓርቲዎችና ሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት አድርገው በሙሉ ትኩረትና አቅም በምርጫው ከተሳተፉ በሕዝብ የተጠላውን የወቅቱን አገዛዝ ከስልጣን ሊያስወግዱት ይችላሉ። በአገዛዙ አይን-አውጣ አፈና ምክንያት ምርጫውን ማሸነፍ ሳይቻል ቢቀር እንኳ ቢያንስ አገዛዙ “በሕዝብ የተመረጥኩ ህጋዊ የሕዝብ መንግስት ስለሆንኩ በኃይል ወይም በሌላ የሽግግር ሂደት አማራጭ ከስልጣን ልወርድ አይገባኝም ” በማለት ዓለምን የሚያጭበረብርበት ን ሰበብ አሳማኝ በሆነ መጠን ከእጁ ማስጣል ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ውጤትም በአንድ በኩል ትግሉን ወደ ሌላ የላቀ ድል ለማሸጋገር፤ በሌላ በኩልም አገሪቱን “ከምጽአተ- ኢትዮጵያ ” የማዳን ዕድል ሊፈጥርልን ይችላል።

ከሁሉም በላይ የጋራ ማንነታችን ስለሆነው ኢትዮጵያዊነትና ለዘላቂ ውጤት ሊያበቃን ስለሚችለው የሰላማዊ ትግል ስልት ያለን አመለካከት ከልብ ካልተቀየረ በስተቀር የሕዝቡ ትግልና መስዋዕትነት እንደተለመደው ከንቱ ሆኖ ከመቅረት የተለየ ውጤት ሊያመጣ አይችልም። አሁን ላይ ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ማንነትን መሰረት አድርጎ በአንድ ሕዝብ ላይ የሚደርስን መዋቅራዊ የኃይል ጥቃት በማንነት ተደራጅቶም ሆነ ጠብመንጃ አንስቶ መታገልን ስህተት ነው ብሎ ማውገዝ የማይቻል ነው። ምክንያቱም ለዚህ ክስተት መፈጠር ዋናው ተጠያቂ አፈናንና ጦርነትን የአገዛዝ ዋና ስልቱ አድርጎ እየተጠቀመ ያለው መንግስት በመሆኑ ነው።

ይህንን እውነታ ብቸኛ ሰበብ ወይም ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያዊነት መደራጀትንም ሆነ በሰላማዊ ስልት መታገልን የማያዋጣ ምርጫ አድርጎ ለማውገዝ መሞከር ግን ትልቅ ስህተት ነው። በእኔ እይታ የወቅቱ የአገራችን ቁልፍ የፖለቲካ ችግር በራሳችን ምርጫም ሆነ ከአቅም በላይ በሆነ አስገዳጅ ሁኔታ ተገፍተን የብሄር አደረጃጀትንና የትጥቅ ትግልን ዋና (ዛሬ ላይ ብቸኛ በሚባል መጠን) የመታገያ ስልቶቻችን እንዲሆኑ ማድረጋችን፣ በአንፃሩ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት መደራጀትንና በሰላማዊ ስልት መታገልን ከዓለም እውነታ በተፃራሪ ስህተትና ኋላ-ቀር አድርገን ማየታችን ነው።

በአጠቃላይ በብሄር ማንነት ተቧድኖ ፖለቲካን ማካሄድ የትኛውንም አገር ሲጠቅም እንዳልታየው ሁሉ፣ በአባቶቻችንና በአያት ቅድመ-አያቶቻችን ዘመን ያልሰራና ዓለም የተጠየፈው የጦርነት አማራጭም በሆነ ተዓምር የኛ ዘመን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በአገራችን ማንነትን መሰረት ያደረገ የኃይል ጥቃት በአስቸኳይ ቆሞ የአገራችን ፖለቲካ ወደ ዜግነት፣ አጀንዳ ተኮር አደረጃጀት እና ሰላማዊ የትግል ስልት ካልገባ በስተቀር ከፊታችን የሚጠብቀን ውጤት “ምፅአተ-ኢትዮጵያ ” ከመሆን የተለየ አይሆንም።
ይሁንና አንዳንድ በስሜትና በምኞት የሚኖሩ ወገኖች “ምጽአተ-ኢትዮጵያ ” ከፊታችን እየመጣ ነው ሲባል አባባሉን “ተራ ሟርት” አድርገው ከማየት ባለፈ በቀላሉ አይረዱትም ። “ምጽአተ-ኢትዮጵያ ” ማለት ሌላ አይደለም። የተያያዝነውን የመፍረስ ሂደት አንድ ቦታ ላይ ካላስቆምነው በስተቀር መዳረሻችን የሚከተለው ይሆናል እንደማለት ነው።

በእኔ ዕይታ (አገሪቱ በያዘችው መንገድ ከቀጠለች) ኢኮኖሚያችን አጠቃላይ ኪሳራ /Total-Bankruptcy/ ውስጥ ይገባል። አገሪቱ አዳዲስ ስራ መፍጠርም ሆነ ኢንቨስትመንት መሳብ አትችልም ። ስራ አጥነት በከፍተኛ መጠን ይስፋፋል፣ የኑሮ ውድነቱም የሕዝቡን የእለት-ተዕለት ኑሮ ወደሚፈታተንበት ደረጃ ይሸጋገራል። እንዲህ ዓይነቱን የኢኮኖሚ ውድቀት ተከትሎም አገሪቱ እዳ መክፈልና አዲስ ብድር ማግኘት የማትችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ። መንግሥትም በዙሪያው ለሰበሰባቸው አድርባዮች ያስለመደውን
ጥቅም ማከፋፈል፣ በስሩ ለሚገኘው ሰራተኛ ደመወዝ መክፈል፣ ለሠራዊቱም ስንቅና ትጥቅ የማቅረብ አቅም ያጣል። ስርዓት አልበኝነትና ሙስናም በከፍተኛ መጠን ይባባሳል። በሂደትም ማዕከላዊ መንግሥቱ ይዳከማል፣ አብዛኛው የአገሪቱ ግዛትም በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎችና የጎበዝ አለቆች እጅ ይወድቃል። መንግስት ም ግብርና ቀረጥ ከሕዝብ መሰብሰብ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ይህን ተከትሎም ውስጣዊና ውጫዊ ጫናን መቋቋም የሚሳነው መንግስት ለይቶለት ይፈርሳል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መሳሪያቸውን እንደያዙ ይበተናሉ። በየብሔር ማንነታቸው እየተቧደኑ አማጺያንን ይቀላቀላሉ፣ አሊያም ሽፍታና ቀምቶ-አዳሪ ይሆናሉ። በጋራ አጀንዳ መተባባር የተሳናቸው አማጺያንም ማዕከሉን ለመቆጣጠር እርስ-በርስ መዋጋት ይጀምራሉ ። አዲስ አበባና አካባቢዋ ዋና የጦርነት አውድማ ይሆናሉ።

የውጭ ኤምባሲዎች አገሪቱን ለቀው ይወጣሉ፣ አገሪቱም ከውጭው ዓለም ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይቋረጣል ። የአየር በረራ ይቆማል፣ የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነት ይቋረጣል፣ የድንበር ላይ ኬላዎች ይፈርሳሉ። ተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ የተትረፈረፈ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች ከአገር መውጣት አይችሉም። የባንኮች መዋቅርም ስለሚፈርስ ከውስጥ ወደ ውጪ ገንዘብ ለማሸሽም ሆነ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ለተቸገረ ዘመድ ገንዘብ መላክ የማይቻል ይሆናል።

አገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በታሪኳ አይታው ወደማታውቀው ዓይነት መንግስት -አልባነትና የእርስ-በርስ ጦርነት ውስጥ ትገባለች። ከተሞቿና የመሰረተ-ልማት አውታሮቿ ይፈራርሳሉ። እያንዳንዱ ዜጋና ቤተሰብ ደህንነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል። ጉልበት ያለው ጉልበት የሌለውን እየዘረፈ ይበላል። ብዙ ሚሊዮኖች በጦርነት፣ በበሽታና በረሃብ ያልቃሉ። ዕድለኛ ሆነው ከሞት የተረፉና አቅሙ ያላቸው ዜጎችም እግሬ- አውጭኝ ብለው ወደ ጎረቤት አገሮች በገፍ ይሰደዳሉ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚከሰተው እልቂትና መሰደድ በዓይነቱም በመጠኑም ወደር የሌለውና ዓለምን በድንጋጤ የሚያስደምም ይሆናል። ከዚህ ሁሉ ውድመትና እልቂት በኋላ ኢትዮጵያ እንደገና አገር የመሆን ዕድል ይኖራታል ? ይህ- አሁን ላይ ማናችንም በቀላሉ ልንመልሰው የማንችል የሚሊየን ዶላር ጥያቄ ይሆናል።

መደምደሚያ

አንዳንድ ሰዎች በተለምዶ ሲሉት እንደሚሰማው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው “በመስቀለኛ መንገድ” ላይ አይደለም ። እንኳንስ በመስቀለኛ፣ ሁለተኛ ምርጫ በሚሰጥ መንታ መንገድ ላይም አይደለችም ። አሁን ላይ እተጓዘች የምትገኝበት መንገድ መዳረሻው “ምጽአተ-ኢትዮጵያ ” መሆኑ አስቀድሞ በታወቀ “ነጠላ መንገድ” /One-way road/ ላይ ነው። ከዚህ በቅርብ ወይም በሩቅ አፍጥጦ ከፊታችን እየጠበቀን ከሚገኝ “ምጽዓተ-ኢትዮጵያ ” ለመዳን ከፈለግን እየተጓዝን ባለንበት መንገድ ላይ “ቀኝ-ኋላ የመዞር” /U-turn/ ያክል አቅጣጫን የመቀየር ብቸኛና ደፋር ውሳኔ ይጠበቅብናል። በአጠቃላይ የወቅቱ ትግል ራሱን በሃቅና በድፍረት ገምግሞ ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረታዊ ድክመቶቹ ን አሳማኝ በሆነ መጠን መፍታት እስካልቻለ ድረስ፣ አሁን እየታየ እንዳለው በፍላጎትና በስሜት ብቻ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድ፣ ለድርድር ማስገደድ፣ ወይም ትግሉን ለዘላቂ ውጤት እንዲበቃ ማድረግ አይቻልም ። ተቃዋሚው ጎራ ከቀድሞዎቹም ሆነ ከራሱ የቅርብ ጊዜ ስህተቶች ተገቢ ትምህርት ቀስሞና የራሱን የቤት-ስራ በአግባቡ ሰርቶ እስካልተገኘ ድረስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አገዛዛቸው በራሳቸው ውስጣዊ ችግሮች በአጭር ጊዜ፣ አልያም በሕዝቡ ትግል በረዥም ጊዜ ከስልጣን ቢወገዱ እንኳን የአጠቃላይ የአገሪቱና የሕዝቡ ህልውና አስተማማኝ ዋስትና ሊኖረው አይችልም ።

እርግጥ ነው አሁን ላይ እየተካሄዱ ያሉት ጦርነቶችና በተለያየ መንገድ ሕዝቡ እያካሄዳቸው ያሉ ትግሎች ህዝባዊ ድጋፍ ያላቸው ስለሆኑ በአገዛዙ ሊሸነፉ አይችሉም ። አለመሸነፍ ብቻም ሳይሆን አገዛዙን በስነ- ልቦና፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እንዲዳከም የማድረግና በሂደትም የማፍረስ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ይሁንና የሚገኘው ውጤት አገዛዙን ከማዳከምና ከማፈራረስ ባለፈ ሕዝቡን ከእልቂት፣ አገሪቱን ከመፈራረስ ማዳን አስካልቻለ ድረስ የወቅቱ የትግል ሂደት እንደ ችግራችን አካል እንጂ እንደ መፍትሄ ሊታይ አይገባውም። መፍትሄ እንዲሆን ከተፈለገ ከላይ የተዘረዘሩት አስር መሰረታዊ ድክመቶች ትርጉም ባለው መጠን መፈታት አለባቸው።

በእኔ በኩል የፖለቲካ ትግል ታሪክን በንባብ በመመርመር፣ ከሁሉም በላይ ካለፉት 31 ዓመታት የራሴ የትግል ተሳትፎና ተሞክሮ በቅን ልቦና ለመማር በመሞከር እንዲህ አይነቱ አቋም ላይ ለመድረስ ችያለሁ። በዚህ የእኔ ግምገማና አቋም የማትስማሙ ብዙዎች እንደምትሆኑ ከመገመት ባለፈ በእርግጠኝነት አውቃለሁ ። አንዳንዶቻችሁም “ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን አገር ስለሆነች፣ ወይም ኢትዮጵያ ን ይህ ትውልድ ጠፍጥፎ ስላልሰራት አንተ እንደምትገምተው በቀላሉ በዚህ ትውልድ አትፈርስም” የሚል የተለመደ ክርክር ልታቀርቡ ትችላላችሁ ።

ይሁንና አንዳችን ስለሌላችን መጠቃት ተቆርቋሪ መሆን አቁመን የእኛ ለምንለው ብሔር ብቻ አልቃሽ የሆንነው፣ ከዚያም አልፈን በብሔር ተቧድነን እርስ-በርስ በጭካኔ እየተገዳደልን የምንገኘው፣ እንዲሁም አንድ አገር ያለን መሆኑን ረስተን በግዛት ጥያቄ መዋጋትና መገዳደል የጀመርነው ያለ ምክንያት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት አዕምሯችን ውስጥ ስለፈረሰ ነው። ያለ ኢትዮጵያዊነት የምትቀጥል ኢትዮጵያ ደግሞ አትኖርም። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ “አትፈርስም ” የምንላት ኢትዮጵያ ከተራ ተስፋና ምኞት ባለፈ “የትኛው ለሷ ተቆርቋሪ የሆነ የፖለቲካ ወኪል ኖሯት ነው ታግሎ ከመፍረስ የሚያድናት ?”

“ኢትዮጵያ አትፈርስም ” የምትሉ ክርክራችሁ በፖለቲካዊ አመክንዮ ያልታገዘና ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ብገነዘብም እኔ ለአገሬ ኢትዮጵያ የምመኝላት ግን የእኔ ግምገማና ግምት ስህተት እንዲሆንና የእናንተ በጎ ምኞትና ፍላጎት እውን እንዲሆን ነው።

ልደቱ አያሌው ታህሳስ 16 / 2016 ዓ.ም


ከጽሑፉ የተወሰዱና ለውይይት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ አከራካሪ ሃሳቦች
  1. ተቃዋሚው ጎራ ራሱን በድፍረት የመገምገምና ውስጣዊ ችግሮቹን የማረም ድክመት አለበት። ይህ ድክመትም ለአገዛዙ እድሜ መራዘም ዋና ምክንያት ሆኗል።
  2. ተቃዋሚው ጎራ ራሱን ገምግሞ ድክመቶቹን ከላረመ በስተቀር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለረዥም ዓመታት በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድል ሊኖራቸው ይችላል።
  3. ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚው ጎራ አሁን በያዙት አካሄድ ከቀጠሉ ሕዝቡ ከእልቂት፣ ኢትዮጵያም
    ከመፍረስ አትድንም።
  4. ለ2019 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች ከወዲሁ መዘጋጀትና መሳተፍ አለባቸው።
  5. የትጥቅ ትግል ለዘላቂ ውጤትና ለውጥ ሊያበቃን አይችልም።
  6. በኢትዮጵያዊነት ወይም በፖሊሲ ተኮር አጀንዳ ተደራጅቶ መታገል ለአገሪቱ የበለጠ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።
  7. አገራዊ ህልውናን ከመፍረስ ለማዳን ከሚደረግ ትግል በመለስ ያሉ ሌሎች ማናቸውም ዓይነት አወዛጋቢ ጥያቄዎች በሙሉ ለጊዜው ወደ ጎን መቆየት አለባቸው።
  8. አገዛዙ ሕዝቡን እርስ-በርስ በማዋጋትና በማደህየት ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ የሚያምን ነው።
  9. ብልጽግና ፓርቲ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነጠቀውን ስልጣኑን መልሶ በእጁ ካስገባና ለሃቀኛ ድርድር ዝግጁነቱን ከገለፀ የአገሪቱ የመፍትሄ አካል ተደርጎ ሊታይ ይገባል።
  10. በሠላማዊ መንገድም ሆነ በጦርነት ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ሃይሎች ሁልጊዜም
    ከአገዛዙ ጋር ሊካሄድ የሚችልን የድርድር አማራጭ ዝግ ማድረግ የለባቸውም።
  11. ሁሉን አቀፍና ሃቀኛ የሆነ አዲስ የሽግግር ሂደት መጀመር የሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ቀዳሚ የጋራ አጀንዳ መሆን አለበት።
  12. በእስካሁኑ የትግል ሂደት አሸናፊ ለመሆን ያልበቁ አመራሮች ከወቅቱ የትግል ሜዳ የአመራርነት
    ሚና ገለል ሊደረጉና አዲሱ ትውልድ የራሱን ዘመን ትግል በራሱ የመምራትና የመወሰን ዕድል ማግኘት አለበት።
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply